በክልል ክለቦች ሻምፒዮና ጥፋተኛ በተባሉ አካላት ላይ ቅጣት ሲተላለፍ ቦዲቲ ወደ ውድድር እንዲመለስ ተወስኗል

የክልል ክለቦች ሻምፒዮና አወዳዳሪ አካል ባለፈው ሐሙስ በተካሄደው የሎጊያ ሰመራ እና ሐረር ቡና ጨዋታ ላይ ከሥነ-ምግባር ውጭ የሆነ ተግባር አሳይተዋል ባላቸው አካላት የጥፋት ውሳኔ አስተላልፏል።

በዚህም መሰረት ሰመራ ሎጊያ ከውድድሩ እንዲታገድ ሲወሰን በርከት ባሉ የቡድኑ አባላት ላይ ደግሞ የቅጣት ውሳኔ እና ማስጠንቀቅያ ሰጥቷል። በተጠቀሰው ጨዋታ ላይ ረብሻው እንዲረጋጋ እና ተጫዋቾቻቸው ከፀብ እና ከድብደባ ድርጊት እንዲቆጠቡ ጥረት አድርገዋል የተባሉት የሰመራ ሎግያ አሰልጣኝ መሐመድ ሁሴን በአወዳዳሪው አካል ምስጋና ደርስዋቸዋል። ከዚህ በተጨማሪ የሰመራ ሎጊያን ውሳኔ በመቃወም በዛሬው ዕለት በነበረበት ጨዋታ ላይ ያልተገኘው ሌላው የአፋር ክልል ተወካይ አሳይታ ከተማም በፎርፌ እንዲሸነፍ አወዳዳሪው አካል ወስኗል። በዚህም አቃቂ ማዞርያ ጨዋታውን በፎርፌ ማሸነፍ ችሏል።

ሌላው ውሳኔ የተሰጠበት ጉዳይ ባለፈው ሳምንት ካለ አግባብ ከውድድር ታግጃለው በሚል ቅሬታ አቅርቦ በነበረው ቦዲቲ ከተማ ሲሆን አወዳዳሪው አካል ጉዳዩን ከመረመረ በኃላ ወደ ውድድር እንዲመለስ ወስኗል።

ለበለጠ መረጃ አወዳዳሪው አካል ጥፋተኛ ናቸው ላላቸው አካላት የሰጠው የውሳኔ ደብዳቤ ይመልከቱ።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡