ኢትዮጵያ የዓለም ዋንጫ ቅድመ ማጣርያ ተጋጣሚዋን ነገ ታውቃለች

በካታር አስተናጋጅነት በ2022 ለሚከናወነው የዓለም ዋንጫ የአፍሪካ ዞን ማጣርያ ድልድል ነገ በግብፅ መዲና ካይሮ ይወጣል።

ወርሀዊ የፊፋ ደረጃን መሰረት ያደረገው የማጣርያ አካሄድ የቅድመ ማጣርያ፣ የምድብ ማጣርያ እና የመለያ (Play-off) ሒደቶች ሲኖሩት በሀገራት ደረጃ ከዝቅተኞቹ የምትመደበው ኢትዮጵያ የቅድመ ማጣርያ ጨዋታ ይጠብቃታል።

በወቅታዊ ደረጃዋ 150ኛ ላይ የተቀመጠችው ኢትዮጵያ ነገ በሚወጣው ድልድል በቋት አንድ ከተመደቡት ዚምባብዌ፣ ሞዛምቢክ፣ ሴራሊዮን፣ ናሚቢያ፣ ጊኒ ቢሳዋ፣ ማላዊ፣ ቶጎ፣ ሱዳን፣ ሩዋንዳ፣ ታንዛኒያ፣ ኢኳቶርያል ጊኒ፣ ኢስዋቲኒ እና ሌሶቶ መካከል ከአንዱ ብሔራዊ ቡድን ጋር የቅድመ ማጣርያ ጨዋታዋን ታደርጋለች። በደርሶ መልስ ማሸነፍ ከቻለችም ወደ ምድብ ማጣርያ ከሚካተቱ 14 ሀገራት መካከል ትሆናለች።

የ2022 ዓለም ዋንጫ ማጣርያ አካሄድ

– 26 ከፍ ያለ የፊፋ ደረጃ ያላቸው ቡድኖች በቅድመ ማጣርያው የማይሳተፉ ሲሆን በቀጥታ ወደ ምድብ ድልድል ያመራሉ።

– ቀሪዎቹ 28 ቡድኖች ባላቸው የፊፋ ወቅታዊ ደረጃ መሠረት ከፍተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ 14 ቡድኖች ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ከሚገኙ 14 ቡድኖች ጋር በቅድመ ማጣርያ ተጫውተው አሸናፊ 14 ብሔራዊ ቡድኖች ወደ ምድብ ድልድል ያመራሉ።

– በድምሩ 40 ብሔራዊ ቡድኖች (26 በቀጥታ፣ 14 በቅድመ ማጣርያ የገቡት) በ10 ምድቦች ተከፋፍለው ይጫወታሉ።

– ከየምድቡ ቀዳሚ ደረጃ ይዘው የሚያጠናቅቁ 10 ሀገራት እንደየደረጃቸው ከፍተኛው ከ ዝቅተኛው ጋር በሚደረግ ድልድል እርስ በርስ የመለያ ጨዋታ ተጫውተው አሸናፊዎቹ 5 ብሔራዊ ቡድኖች ወደ ካታሩ የዓለም ዋንጫ ያመራሉ።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡