በቻን 2020 ቅድመ ማጣርያ የመልስ ጨዋታ የኢትዮጵያ እና የጅቡቲ ብሔራዊ ቡድኖች የመልስ ጨዋታ ነገ በድሬዳዋ ስታዲየም ይደረጋል።
ሁለቱ ቡድኖች የመጀመርያ ጨዋታቸውን ጁቡቲ ላይ ባሳለፍነው ሳምንት አከናውነው ኢትዮጵያ በአስቻለው ታመነ ከእረፍት መልስ በተገኘች የፍፁም ቅጣት ምት ጎል 1-0 በማሸነፍ መመለሷ የሚታወስ ሲሆን የመልሱን ጨዋታ ለማድረግ ሁለቱም ብሔራዊ ቡድን ከሰኞ ጀምሮ ጨዋታውን በሚያደርጉበት ድሬዳዋ ዝግጅታቸውን ሲያደርጉ ቆይተዋል።
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በኩል አቤል ያለው እና አቡበከር ናስር ባጋጠማቸው ጉዳት ከብሔራዊ ቡድኑ ስብስብ ውጭ ከሆኑበት አጋጣሚ በቀር ሁሉም ተጫዋቾች ለነገው ጨዋታ ዝግጁ መሆናቸው ተረጋግጧል። ብሔራዊ ቡድኑ ቀለል ያለ የመጨረሻ ልምምድ ይሰራል ተብሎ ቢጠበቅም ሳይሰራ ሲቀር ይልቁንም በሆቴላቸው የንድፈ ሀሳብ ትምህርቶችን ሲከታተሉ ውለዋል።
በወጣት ተጫዋች በተገነባው የጅቡቲ ብሔራዊ ቡድን 23 ተጫዋቾችን በመያዝ በፈረንሳዊው አሰልጣኝ ዡሊያን ሜት እየተመሩ ጠንከር ያለ ልምምዳቸውን ከረፋዱ 10:00 ጀምሮ ለአንድ ሰዓት በመቆየት አከናውነዋል። በቡድኑ ውስጥ አስቀድሞ በናሽናል ሲሚንት ሲጫወት የምናቀው መሐሙድ መሐመድ በመጀመርያው ጨዋታ ላይ ባጋጠመው ጉዳት ከነገው ጨዋታ ውጭ መሆኑ ሲረጋገጥ በድሬዳዋ ዋናው ቡድን የመጫወት ዕድል ባያገኝም ከቡድኑ ጋር አብሮ ለሦስት ዓመት የቆየው አብዲ መሐመድ በዛሬው ልምምድ ላይ ከቡድኑ ጋር ተቀላቅሎ ልምምድ አለመስራቱ በነገው ጨዋታ ላይ የመሰለፉ ነገር አጠራጣሪ ሆኗል። ከዚህ ውጭ አብዛኛው የቡድኑ አባላት ለነገው ጨዋታ ዝግጁ መሆናቸውን ለመመልከት ችለናል።
የጅቡቲው አሰልጣኝ ዡልያን ሜት ስለ ነገው ጨዋታ ሲናገሩ ” ወደ ድሬዳዋ ከመጣን አንድ ሳምንት ሆኖናል። በዚህ ቆይታችን በመጀመርያው ጨዋታ ላይ የነበሩብን ጠንካራ እና ደካማ ጎናችንን በቪዲዮ በተደጋጋሚ ተመልክተን ድክመቶቻችን ላይ ሰርተናል። ለነገ ጨዋታም የሚሆን በቂ ዝግጅት አድርገናል፣ የመጀመርያው ጨዋታ ከጉዳት ጋር በተያያዘ ካልተጠቀምንባቸው ተጫዋች ውጪ አዲስ ጉዳት ሆነ ቅጣት የለብንም። የጅቡቲ እግርኳስ በእንቅልፍ ውስጥ ይገኝ ነበር፤ አሁን ግን ያለፉትን ሁለት እና ሦስት ወራት በጥሩ መነቃቃት ይገኛል። ዓላማችን የአፍሪካ ዋንጫ መግባት ነው። ሰሞኑን ድሬዳዋ እየዘነበ በመሆኑ ባልለመድነው አየር ውስጥ ነው የምንገኘው። ነገ ምን ዓይነት አየር ንብረት እንደሚፈጠር ባናቅም። በየትኛውም አየር ንብረት ውስጥ የምንፈልገውን ውጤት ይዘን ለመውጣት የተዘጋጁ ወታደሮች አሉኝ። በጨዋታውም 2-1 አሸንፈን ወደ ቀጣዩ የመጨረሻ ማጣርያ ለማለፍ ተዘጋጅተናል።” በማለት ተናግረዋል።
ጨዋታው ነገ 10:00 በድሬዳዋ ስታዲየም የሚካሄድ ሲሆን ጨዋታውን ሶማሊያዊያን ዳኞች የሚመሩት ይሆናል።
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡