የአንደኛ ሊግ የማጠቃለያ ውድድር በባቱ ከተማ አሸናፊነት ተጠናቀቀ

ከሐምሌ 7 ጀምሮ ለአስራ አምስት ቀናት በ18 ቡድኖች መካከል በባቱ (ዝዋይ) ሲካሄድ የቆየው እና ወደ ከፍተኛ ሊግ ያደጉ ስድስት ቡድኖችን የለየው የአንደኛ ሊግ የ2011 የማጠቃለያ ውድድር በዕለተ ሰኞ በባቱ ከተማ አሸናፊነት ተጠናቋል።

07:00 ላይ አስቀድሞ በተካሄደው የደረጃ ጨዋታ ጋሞ ጨንቻ ሶሎዳ ዓድዋን 1-0 በሆነ ጠባብ ውጤት በማሸነፍ ሦስተኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቋል። ሁለቱም ቡድኖች ለፍፃሜ ለማለፍ በተጋጣሚዎቻቸው ተሸንፈው ለደረጃ ጨዋታ እንደመድረሳቸው መጠን የመጫወት ፍላጎታቸው እና እንቅስቃሴያቸው የቀዘቀዘ ነበር። በዘጠና ደቂቃ ውስጥ በጎል ሙከራው ረገድ የጋሞ ጨንቻው አጥቂ በድሉ ሰለሞን ከፈጠራቸው ሁለት የጎል አጋጣሚዎች በቀር ሌሎች ሙከራዎችን መመልከት አልቻልንም። 

በመሐል ሜዳ እና አልፎ ወደ ፊት በሚሄደው በዚህ ጨዋታ ከእረፍት መልስ ተቀይሮ እንደገባ ከአንድ ደቂቃ በኃላ 49ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ መስመር የተሻገረውን ኳስ ንዋይ ተሾመ አግኝቶ ወደ ጎልነት በመቀየር ጋሞችን የማሸነፊያ ብቸኛ ጎል አስቆጥሯል። ለዚህች ጎል መቆጠር ቀድሞ አርባምንጭ ከተማ ዋናው ቡድን አጥቂ የነበረው ፍሬው አለማየሁ አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነበር። ጨዋታውም የተለየ ነገር ሳያስመለክተን በጋሞ ጨንቻ 1-0 አሸናፊነት በመጠናቀቁ ጋሞ ጨንቻ ሦስተኛ ደረጃ በመያዝ ውድድሩን አጠናቋል።

09:00 በቀጠለው የፍፃሜ ጨዋታ ኮልፌ ቀራንዮን ከባቱ ከተማ ያገናኘው ጨዋታ መደበኛው ክፍለ ጊዜ አንድ አቻ በመጠናቀቁ በመለያ ምት ባቱ ከተማ 5-4 አሸንፎ የውድድሩ አሸናፊ በመሆን የዋንጫ ተሸላሚ ሆኗል። የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝደንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ እና የባቱ ከተማ ከፍተኛ አመራሮች በመዝጊያው ጨዋታ ላይ በክብር እንግድነት ተገኝተዋል። በርካታ ተመልካች በተከታተለው በዚህ ጨዋታ የመጀመርያው አጋማሽ የሚቆራረጡ ኳሶች የበዙበት እና የጥንቃቄ አጨዋወት መሠረት ያደረገ ነበር። በውድድሩ ላይ የመጀመርያ ጨዋታውን በሽንፈት ቢጀምርም ከጨዋታ ጨዋታ ቅርፅ እየያዘ የመጣው እና በወጣት ተጫዋቾች የተደራጀው ኮልፌ ቀራኒዮ ከባቱ ከተማ በኳስ ቁጥጥሩ የተሻለ መንቀሳቀስ ችለዋል። በበርካታ ደጋፊዎቻቸው የታጅቡት እና በአምበላቸው ብርሃኑ ሆራ ልምድ የሚመሩት ባቱዎች በመስመር አጨዋወት የጎል እድል ለመፍጠር ጥረት ቢያደርጉም ጎል ማስቆጠር አልቻሉም።

ከእረፍት መልስ ተመጣጣኝ የሆነ ጥሩ ፍሰት ያለው እግርኳስ መመልከት የቻልንበት ጨዋታ ነበር። በተረጋጋ ሁኔታ በራሳቸው የሜዳ ክፍል ኳሱን ተቆጣጥረው በፍጥነት ወደ ፊት በመሄድ አደጋ በመፍጠር ሲጫወቱ የቆዩት ኮልፌዎች በ67ኛው ደቂቃ በያሬድ ወንድማገኝ አማካኝነት ጎል አስቆጥረው መምራት ችለዋል። ይህች ጎል ሲቆጠር በስታዲየም ውስጥ የነበሩ በርካታ የባቱ ደጋፊዎች በዝምታ ተውጠው ነበሩ።

ከጎሉ መቆጠር በኃላ ተጭነው የተጫወቱት ባቱዎች ረጃጅም ኳስ ወደ ፊት በመጣል ለፊት መስመር አጥቂያቸው ኳሱን በማድረስ ጎል ለማስቆጠር ያደረጉት ጥረት ተሳክቶ 76 ኛው ደቂቃ ከግራ መሰመር የተሻገረውን የቀድሞ የንግድ ባንክ ተስፋ ቡድን ተጫዋች እና የውድድሩ ጥሩ አጥቂ መሆኑን ያሳየው በላይ ገዛኸኝ በግንባሩ ኳሱን ከመሬት ጋር አንጥሮ ባስቆጠረው ጎል ባቱዎችን አቻ አድርጓል። ይህች ጎል ስትቆጠር በስታዲየሙ ውስጥ የታየው የደስታ አገላለፅ አስገራሚ ነበር። በቀሩት ደቂቃዎች ተጨማሪ ጎል ፍለጋ ባቱዎች በተደጋጋሚ ወደ ፊት ቢሄዱም ተጨማሪ ጎል ማስቆጠር ሳይችሉ ጨዋታው 1-1 አቻ ውጤት በመጠናቀቁ ወደ መለያ ምት አምርቶ ባቱ ከተማ 5-4 በሆነ ውጤት በማሸነፍ የማጠቃለያ ውድድሩ አሸናፊ ሆኗል።

በመጨረሻም የዋንጫ አሰጣጥ ሥነ ስርዓት ተካሂዷል። ከየምድባቸው አንደኛ በመሆን የጨረሱት ሱሉልታ ከተማ፣ ቂርቆስ ክ/ከተማ፣ ባቱ ከተማ፣ ጋሞ ጨንቻ፣ ራያ አዘቦ እና ዳሞት ከተማ ከዕለቱ የክብር እንግዳ እያንዳንዳቸው የዋንጫ ተሸላሚ ሆነዋል። በመቀጠል የአንደኛ ሊግ ማጠቃለያ ውድድር ከአንድ እስከ ሦስት ለወጡት ሜዳልያቸውን ከወሰዱ በኋላ የውድድሩ አሸናፊ የሆነው ባቱ ከተማ በአምበሉ ብርሃኑ ሆራ አማካኝነት የዕለቱን ዋንጫ አንስተዋል። የስፖርታዊ ጨዋነት አሸናፊ ደግኞ ጋሞ ጨንቻ ሆኗል።

* ለአስራ አምስት ቀናት በ18 ቡድኖች መካከል በባቱ (ዝዋይ) በተሳካ ሁኔታ ሲካሄድ የቆየው የ2011 የአንደኛ ሊግ የማጠቃለያ ውድድር ከመቼውም ጊዜ በተሻለ ጥራት ያላቸው ቡድኖች ከመመልከታችን ባሻገር ከተወሰኑት ክለቦች በቀር በአብዛኛው ማለት በሚቻል ሁኔታ ወጣት ተጫዋቾችን ይዘው የቀረቡ መሆኑ ይህን ውድድር የተለየ ያደርገዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡