ከነዓን ማርክነህ በጊኒ የተጫወተ የመጀመርያው ኢትዮጵያዊ በመሆን ቻምፒዮኑ ሆሮያ ክለብን ለመቀላቀል በቅርቡ ወደ ጊኒ ያቀናል።
የጊኒው ሆሮያ ክለብ አሰልጣኝ ዲዲዬ ጎሜስ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከታዩ ጥሩ ክህሎት ካላቸው ተጫዋቾች መካከል አንዱ የሆነው ከነዓንን በጥብቅ ሲከታተሉት ከቆዩ በኋላ በመጨረሻም ለአራት ዓመት የሚያቆየውን የውል ኮንትራት በማስፈረም የግላቸው አድርገውታል። ሆሮያ ከነዓን ለአራት ዓመት የሚቆየውን የረዥም ዓመት ኮንትራት እንዲፈርም መወሰናቸው አሰልጣኝ ዲዲዬ ጎሜስ ከነዓን አሁን ካለበት ወቅታዊ አቋም በተሻለ ሁኔታ ወደ ፊት የሚያድግ አቅም እንዳለው በመተማመን እንደሆነ የከነዓን ወደ ሆሮያ እንዲጓዝ ትልቁን ሚና የተወጣው ቢኒያም ሚዴቅሳ ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግሯል።
ከዚህ በተጨማሪ ከነዓን አሁን ባቀናበት ሆሮያ ክለብ የተሻለ እንቅስቃሴ ማሳየት ከቻለ ወደ አውሮፓ ወጥቶ እንዲጫወት ዕድል እንደሚያመቻቹለት ሰምተናል። ያለ ሙከራ በቀጥታ ፊርማውን ያኖረው ከነዓን ዛሬ አልያም ነገ የአውሮፕላን ትኬቱ ከተመቻቸ በኃላ ወደ ጊኒ የሚያቀና ይሆናል።
በአዳማ ተስፋ ቡድን የእግርኳስ ህይወቱን መነሻው ያደረገው ከነዓን በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ እና በአዲስ አበባ ከተማ ክለብ ከመጫወቱ ባሻገር ያለፉትን ሁለት ዓመታት በአዳማ ከተማ ድንቅ የውድድር ጊዜ በማሳለፍ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በወጣት እና በዋናው ቡድን እየተጫወተ ይገኛል።
የጊኒ የጥምር ዋንጫ አሸናፊው ሆሮያ ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ ከ7 ዓመታት በላይ ቆይታ ያደረገው ዩጋንዳዊው ሮበርት ኦዶንካራን የግሉ ማድረጉ የሚታወስ ነው።
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡