ሰበታ ከተማ አዲስ አሰልጣኝ ለመቅጠር ከጫፍ ደርሷል

ሰበታ ከተማ ከአሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተና ጋር ሳይስማማ ሲቀር አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነ ማርያም ክለቡን በቅርቡ እንደሚረከቡ ይጠበቃል።

ከስምንት ዓመታት በኋላ በአሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተና መሪነት ወደ ፕሪምየር ሊጉ ያደገው ሰበታ ከተማ ከአሰልጣኙ ጋር የሁለት ወራት ኮንትራት ቢቀረውም ሁለቱ አካላት መስማማት አለመቻላቸውን አሰልጣኝ ክፍሌ በተለይ ለሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጠዋል፡፡ “ዛሬ ጠዋት ጠርተው አናግረውኝ ነበር። እስካሁን ሳይነግሩኝ ቀርተው ክለቦች ማስታወቂያ ሲያወጡ አስቀድሜ መወዳደር እየቻልኩ ዛሬ ጠርተው እንደማልቀጥል ሲነግረኝ ተከፍቻለሁ። ከክለቡ ጋር የሁለት ወር ቀሪ ውል አለኝ። ነገር ግን በተፈጠረው ሁኔታ ምክንያት ሳንስማማ ቀርተናል።” ብለዋል፡፡

ሰበታ ከተማ በክለቡ የመቀጠላቸው ጉዳይ አጠራጣሪ በሆኑት ክፍሌ ቦልተና ምትክ አዲስ አለቃ ለመሾም እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ ከዳር መድረሱ ሲረጋገጥ ፀጋዬ ኪዳነ ማርያምን ቀጣዩ አሰልጣኝ ለማደረግ መቃረቡም ታውቋል። የቀድሞው የትራንስ፣ ሐረር ቢራ፣ ኢትዮጵያ ቡና፣ ንግድ ባንክ፣ አርባምንጭ ከተማ እና ወልዋሎ አሰልጣኝ ያለፉትን አምስት ወራት ያለ ስራ የዘለቁ ሲሆን ከሰበታ ጋር በቃል ደረጃ ከስምምነት መድረሳቸውና ከወዲሁ ወደ ዝውውር እንቅስቃሴ በመግባት ከተጫዋቾች ጋር እየተነጋገሩ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡