ሀዋሳ ከተማ የሶስት የውጪ ተጫዋቾችን ውል አራዘመ

በአሰልጣኝ አዲሴ ካሳ እየተመራ ካለፉት ዓመታት አንፃር የተሻለ ነጥብን በመሰብሰብ በደረጃ ሰንጠረዡ ስድስተኛ ሆኖ የዘንድሮው የውድድር ዘመንን ያጠናቀቀው ሀዋሳ ከተማ አዳዲስ ተጫዋቾችን በማስፈረም እና ነባሮችን በማቆየት ስራ ላይ ይገኛል፡፡ ዘንድሮ በደቡብ ፖሊስ ጥሩ ጊዜ ያሳለፈው አጥቂው ሄኖክ አየለን በአንድ ዓመት ወደ ቡድኑ የቀላቀለ ሲሆን ሦስት ነባር የውጪ ተጫዋቾችን ውል ደግሞ አራዝሟል፡፡

ውል ካራዘሙት ተጫዋቾች መካከል ቀዳሚው ቶጎዊው ግብ ጠባቂው ሶሆሆ ሜንሳህ ነው። የጋቦኑ ሲኤፍ ሞናናን በመልቀቅ በ2009 ወደ ኢትዮጵያ ከመጣ በኋላ በሀዋሳ ከተማ በመደበኝነት እየተሰለፈ የሚገኘው ሶሆሆ ለተጨማሪ አንድ ዓመት ለመቆየት ውሉን አራዝሟል፡፡

ሌላኛው ውሉን ያራዘመው የመሐል ተከላካዩ ጋናዊው ላውረንስ ላርቴ ነው፡፡ በጋናው አሻንቲ ጎልድ እና በደቡብ አፍሪካው አያክስ ኬፕታውን መጫወት የቻለው የ28 ዓመቱ ተከላካይ ባለፉት ሁለት ዓመታት በሀዋሳ ከተለያዩ ተጫዋቾች ጋር በመጣመር ጠንካራ የተከላካይ ክፍል ክለቡ እንዲፈጥር አድርጓል፡፡ ከክለቡ በመለያየት ወደ ፋሲል ከነማ ያመራል የሚሉ መረጃዎች ወጥተው የነበረ ቢሆንም በ2012 በክለቡ መቆየቱን አረጋግጧል፡፡

ያኦ ኦሊቨር ሦስተኛው ውል ያራዘመ ተጫዋች ሆኗል፡፡ ኮትዲቫራዊው የግራ መስመር የኤ ኤስ ታንዳ ተጫዋች የነበረው ተጫዋቹ ዘንድሮ ሀዋሳን ከተቀላቀለ በኃላ በመጀመሪያው ዙር ባሳየው ደካማ አቋም ክለቡ ለማሰናበት ወስኖ የነበረ ቢሆንም አሰልጣኝ አዲሴ ካሳ ተጫዋቹን የሚተካ አማራጭ ማግኘት ባለመቻላቸው በሁለተኛው ዙር እንዲቀጥል አድርገውት በርከት ያሉ ጨዋታዎች ላይ ተሰልፎ በጥሩ ብቃት መጫወት ችሏል፡፡

በተያያዘ ከክለቡ ጋር የነበራቸው ውል የተጠናቀቀው ታፈሰ ሰለሞን፣ ፍቅረየሱስ ተወልደብርሀን እና ተክለማርያም ሻንቆን ውላቸውን በማደስ ለማቆየት እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሆነ አሰልጣኝ አዲሴ ካሳ ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡