ከባለፈው ዓመት ቡድናቸው ሦስት ተጫዋቾች ወደ ሌሎች ቡድኖች የሄዱባቸውና በዝውውሩ በስፋት ይሳተፋሉ ተብሎ የተጠበቁት ወልዋሎዎች ከድሬዳዋ ከተማ ሦስት ተጫዋቾች አስፈርመዋል።
የቡድኑ የመጀመርያ ፈራሚ የመሃል ተከላካይ ፍቃዱ ደነቀ ሲሆን በክለቡ የተከላካይ ክፍል ላይ ተቀዳሚ ምርጫ ይሆናል ተብሎ የሚጠበቅ ተጫዋች ነው። ከዚህ በፊት ከአሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ጋር በሁለት አጋጣሚዎች መስራት የቻለው ተከላካዩ በተለይም በ2009 በመቐለ ባሳየው ወጥነት ያለው ጥሩ ብቃት ይታወሳል። ባለፈው ዓመት በተከላካዮች የተገደበ ምርጫ የተቸገሩት አሰልጣኙ በዚህ ዓመት በተከላካዮች ዝውውር ጀምረውታል።
ሁለተኛው የቡድኑ ፈራሚ የግራ መስመር ተከላካዩ ሳሙኤል ዮሐንስ ነው። ባለፈው ዓመት በሊጉ ከታዩት ተስፈኛ የግራ መስመር ተጫዋቾች አንዱ የሆነው ተጫዋቹ አሰልጣኙ ድሬዳዋ ከተማ በነበሩበት ወቅት ቀዳሚ ምርጫቸው የነበረ ሲሆን በወልዋሎ ቆይታውም ተመሳሳይ ነገር ይጠበቃል። በማጥቃት ላይ ባለው የጎላ ተሳትፎ የሚታወቀው ተጫዋቹ ከዚ በፊት ለአማራ ውሃ ስራና ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መጫወቱ ይታወሳል።
ሦስተኛው የቡድኑ ፈራሚ የመስመር ተጫዋቹ ራምኬል ሎክ ነው። ባለፈው ዓመት ፋሲል ከነማን ለቆ ብርቱካናማዎቹን በመቀላቀል ከጉዳት ጋር እየታገለ ዓመቱን የጨረሰው ተጫዋቹ መቐለ 70 እንደርታን ለተቀላቀለው ኤፍሬም አሻሞ ጥሩ ተተኪ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። ከዚህ ቀደም ለንግድ ባንክ፣ ኤሌክትሪክ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ፋሲል ከነማ እና ድሬዳው ከተማ መጫወት የቻለው ተጫዋቹ እንደ ሁለቱ ተጫዋቾች በድሬዳው ቆይታው በአሰልጣኙ ቀዳሚ ምርጫ የነበረ ሲሆን በብሔራዊ ቡድንም በአሰልጣኙ ስር ሰርቷል።
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡