መቐለ ቡርኪናፋሷዊ አማካይ ለማስፈረም ሲቃረብ ፅዮን መርዕድን ሳያስፈርም ቀርቷል

በዝውውር መስኮቱ ንቁ ተሳትፎ እያደረጉ የሚገኙት የሊግ ቻምፒዮኖቹ ምዓም አናብስት የቡርኪፋሶ ዜጋ ያለው አማካይ ለማስፈረም ሲቃረቡ ከሳምንታት በፊት ለማስፈረም ተስማምተውት ከነበረው ወጣት ግብ ጠባቂ ፅዮን መርዕድ ጋር ተለያይተዋል።

ፍሊፕ ኦቮኖ፣ ሶፎንያስ ሰይፈ እና ምሕረትአብ ገ/ህይወትን በቡድናቸው ውስጥ የያዙት መቐለዎች ከሳምንት በፊት በአርባምንጭ ከተማ ተስፋ ያለው እንቅስቃሴ ያሳየው ፅዮን መርዕድን ለማስፈረም ተስማምተው ከቡድኑ ጋር ልምምድ እየሰራ ቢቆይም በዛሬው ዕለት ከተጫዋቹ ጋር በስምምነት መለያየታቸውን ለማወቅ ተችሏል። መቐለዎች በሳምንቱ መጀመርያ ከአለልኝ አዘነ ጋር በተመሳሳይ ሳይስማሙ መለያየታቸውም የሚታወስ ነው።

ወደ መቐለ 70 እንደርታ ይዘዋወራል ተብሎ የሚጠበቀው ብርኪናፋሷዊ የተከላካይ አማካይ ሙሳ ዳኦ ነው። ዛሬ ከቡድኑ ጋር ልምምድ የጀመረው ተጫዋቹ ስሙ ለቻምፒየንስ ሊግ ጨዋታ ወደ ካፍ መላኩ የታወቀ ሲሆን ምዝገባው ከፀደቀ በይፋ ይፈርማል ተብሏል። ተጫዋቹ ከዚህ በፊት በአል መስሪ ፣ አል ሃማም እና አል ጃራ የተጫወተ ሲሆን በተለይም በ2016\17 በሆሳም ሐሰን እየተመራ በግብፅ ፕሪምየር ሊግ አራተኛ ሆኖ በጨረሰው እና በኮንፌደሬሽን ዋንጫ የተሳተፈው አል ማስሪ ቡድን ጥሩ ጊዜ ነበረው።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡