ሲዳማ ቡና የሰባት ወጣት ተጫዋቾችን ውል አራዘመ

ሲዳማ ቡና ከወጣት ቡድኑ አድገው ውላቸውን የጨረሱ ሰባት ተጫዋቾችን ለተጨማሪ ዓመታት አድሷል።

በዘንድሮው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በአሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ እየተመራ በዋንጫ ፉክክር ውስጥ በመዝለቅ በመጨረሻው ጨዋታ ወልዋሎን በሜዳው በመርታት በሁለተኝነት ደረጃ ያጠናቀቀው ክለቡ በቡድኑ ውስጥ ያሉ ተጫዋቾችን ውል ማራዘምን ቀዳሚው በማድረግ ባለፉት አምስት ዓመታት ከታዳጊ ቡድን መጥተው ውላቸው የተጠናቀቁትን ሰባት ወጣት ተጫዋቾችን ውል ማራዘሙን አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡

ይገዙ ቦጋለ ካደሱት መካከል አንዱ ነው። የፊት መስመር ተሰላፊው ካለፉት ሁለት የውድድር ጊዜያት በተሻለ አቅም ዘንድሮ በክለቡ የቋሚነትን ዕድልን ማግኘት ችሏል፡፡ ከተጠባባቂ ወንበር እየተነሳ ሲጫወት የነበረው ፈጣኑ የመስመር አጥቂ አዲሱ ተስፋዬ ሁለተኛው ውል ያደሰ ተጫዋች ሲሆን አማካዩ ሚካኤል ሀሲሳ ካራዘሙ ተጫዋቾች መካከል ሦስተኛው ነው፡፡

ሌሎች በክለቡ ለተጨማሪ ሁለት ዓመታት ውል ያራዘሙት ክፍሌ ኬአ (አጥቂ)፣ ቢኒያም ላንቃሞ (አማካይ)፣ አማኑኤል እንዳለ (መስመር አጥቂ) እና ለይኩን ነጋሽ (ግብ ጠባቂ) ናቸው።

በቀጣዩ ቀናት የወሳኝ ተጫዋቾቹን ውል አንደሚያራዝም የሚጠበቀው ክለቡ አምስት አዳዲስ ተጫዋቾችን ለማምጣት እንዳቀደም አሰልጣኙ ገልፀዋል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡