ወልቂጤ ከተማ ምክትል አሰልጣኝ እና አንድ ተጫዋች ለማስፈረም ተስማምቷል

አዲስ አዳጊው ወልቂጤ ከተማ አሰልጣኝ ተመስገን ዳናን የደግአረግ ይግዛው ረዳት ለማድረግ ሲስማማ ፍፁም ተፈሪን አምስተኛ ፈራሚው ለማድረግ ከስምምነት ደርሷል፡፡ 
አሰልጣኝ ተመስገን ዳና በሀዋሳ ከተማ ከ17 እና 20 ዓመት በታች ቡድኖችን በማሰልጠን ስኬታማ ጊዜያትን ያሳለፈ ሲሆን ታንዛኒያ ላይ በተካሄደው የሴካፋ የወጣቶች ውድድር ላይ ኢትዮጵያን እስከ ፍፃሜው ማድረስ ችሎ ነበር። አሰልጣኙ በዘንድሮው የውድድር ዓመት የአሰልጣኝ አዲሴ ካሳ ረዳት በመሆን በሀዋሳ ከተማ የሰራ ሲሆን በዓመቱ አጋማሽ ከተለያየ በኃላ የአሰልጣኝ ደግአረግ ረዳት አሰልጣኝ በመሆን ወደ አዲስ አዳጊው ለማምራት መስማማቱን ክለቡ አስታውቋል።

ፍፁም ተፈሪ የአማካይ ስፍራ ተጫዋች ሲሆን የእግር ኳስ ህይወቱን በበርካታ ክለቦች መርቷል። ሀዋሳ ከተማ (በሁለት ጊዜያት)፣ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ደደቢት፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ሲዳማ ቡና የተጫወተው ፍፁም የተጠናቀቀው የውድድር ዓመትን በወላይታ ድቻ አሳልፏል።

በቀጣዮቹ ቀናት ተጨማሪ ተጫዋቾችን ወደ ቡድኑ እንደሚቀላቅል የሚጠበቀው ክለቡ እስካሁን በረከት ጥጋቡ፣ ቶማስ ስምረቱ፣ ብርሀኑ በቀለ እና አንዶህ ኩዌኩን አስፈርሟል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡