“ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ሜዳዎች አንዳቸውም የካፍን መመዘኛ አያሟሉም ተብለናል፡፡”
ካፍ በቅርቡ ባደረገው ግምገማ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ሜዳዎች ዓለም አቀፍ ውድድሮችን የማስናገድ አቅም ላይ የማይገኙ በመሆኑ የቀጣይ የአፍሪካ መድረክ ጨዋታዎችን በሜዳ የመጫወት ሁኔታ ጥያቄ ምልክት ውስጥ ገብቷል።
በኢትዮጵያ ከአዲሱ ሚሌኒየም ወዲህ በመላ ሀገሪቱ ግዙፍ የሚባሉ ስታዲየሞች በመገንባት ላይ ቢሆኑም አንዳቸውም ሙሉ ለሙሉ አልተጠናቀቁም። ከተመልካች መቀመጫዎች እና ውጫዊ ገፅታ ባሻገር የመጫወቻ ሜዳ ጥራት፣ አስፈላጊ ውስጣዊ ግንባታዎች ላይ የሚሰጠው ትኩረት አናሳ መሆኑ ዋጋ እያስከፈለን መጥቷል። በቅርቡ እንኳን በ2020 የቻን ውድድርን ለማስተናገድ በካፍ ተመርጣ የነበረችው ሀገራችን ለሁለት ጊዜያት ሀዋሳ፣ መቐለ፣ ባህርዳር እና አዲስ አበባ የሚገኙ ስታዲየሞችን በካፍ አስገምግማ ያሉበት ወቅታዊ ሁኔታ ውድድሩን ለማስተናገድ ብቁ አይደሉም በሚል የማዘጋጀት ዕድላችንን አሳልፈን ለካሜሩን መስጠታችን ይታወሳል ፡፡
በጉዳዩ ዙርያ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ ጂራ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረጉት ቆይታ “ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ሜዳዎች አንዳቸውም የካፍን መመዘኛ አያሟሉም ተብለናል፡፡” ሲሉ ይናገራሉ ” የአዲስ አበባ ስታዲየምን ከአሁን በኃላ ካፍ መጠቀም አትችሉም ብሎ በደብዳቤ አግዷል። የመቐለን ለማስመዝገብ ልከናል፤ የባህር ዳን አስቀድመን ስላሳወቅን ብቻ ዕድል ሊኖረን ይችላል። አንድ ተስፋችን ባህርዳር ብቻ ሊሆን ነው።” ሲሉም አክለዋል።
እንደ ፕሬዝዳንቱ ገለፃ የሀዋሳ ስታዲየም ሳር በመበላሸቱ በአዲስ ሳር ለመተካት ዕድሳት ላይ የሚገኝ ሲሆን “የአዲስ አበባ ስታዲየም በተለይ የመልበሻ እና የመፀዳጃ ቤቱ እጅጉን የማይመጥን በመሆኑ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን እንዳያስተናግድ ታግዷል።” ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ስታዲየምን በሚመለከት ለጠየቅናቸው ጥያቄ “ለስፖርት ኮሚሽን ደብዳቤ ፅፈናል። ዛሬ ብቻ አይደለም ለስፖርት ኮሚሽን የተፃፈለት። ከኛ በፊት የነበሩት አመራሮች ወቅትም ከአንድም ሦስት ጊዜ ካፍ ይሄ ሜዳ እንዲታደስ አሳስቦ ነበር። ይህ የሀገሪቱ ጉዳይ ነው፤ ፌዴሬሽኑ ሜዳውን ለምን አያድስም የሚል ጥያቄ ሊኖር ይችላል። ነገር ግን ይህ የመንግስት ጉዳይ ስለሆነ ይህንን አሳውቀናል። የፊፋ አባል ሀገር ሆነን ሜዳ የላችሁም መባላችን ለሀገር ውርደት ነው። እኔም ለስራ አስፈፃሚዎቼ እንድታውቁት ብዬ በደብዳቤ አሳውቄያለሁ። በኛ ሀገር ሜዳዎች መሰራታቸው መልካም ቢሆንም በተለይ የመጫወቻ ሜዳዎቹ እጅጉን ደካሞች ናቸው። ” ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ ትላንት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በድሬዳዋ ከጅቡቲ ጋር ሲጫወት ተመልካች ስታዲየም ገብቶ ያለመመልከቱ ከዚህ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ያስረዳሉ “የድሬዳዋ ስታዲየም ገና አልተጠናቀቀም። የግንባታ ዕቃዎች እና የአሸዋ ክምር በሜዳ ውስጥ በመታየታቸው በዝግ እንዲሆን ተደርጓል። ይህን ሳናሟላ ለመጫወት መሞከር አዳጋች ነው። ሜዳው ጥሩ ቢሆንም ግንባታው ባለማለቁ ኮሚሽነሩ ያደረጉት ነገር ትክክል ነበር። ይህ በመሆኑ ግን ተከፍቻለሁ”
በቀጣይ ጊዜያት በዓለም ዋንጫ፣ ቻን፣ አፍሪካ ዋንጫ እንዲሁም የወጣቶች እና ሴቶች ውድድሮች በርካታ ማጣሪያዎች ያሉባት ኢትዮጵያ በሀገሪቱ ያሉ ሜዳዎች ብቁ ባለመሆናቸው ካፍ ባሳለፍነው ማክሰኞ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ደብዳቤ በመላክ ማስጠንቀቁን ኢሳይያስ ጂራ ተናግረዋል። ” ከአሁን በኋላ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚደረጉ ጨዋታዎችን ወደ ጎረቤት ሀገር እንወስድባለኋን ብሎናል። ባለፈው ማክሰኞ ደብዳቤን ልኮልን ካልጨረሳቹ፤ መስተካከል ያለበትን ማስተካከል ካልቻላችሁ ኢንተርናሽናል ጨዋታን በሀገራችሁ አታደርጉም። ወደ ጎረቤት እንወስድባችዋለን ተብለናል። እኛም ለመንግስት ይህን ጉዳይ አሳውቀናል።” ሲሉ ሀሳባቸውን ጠቅልለዋል፡፡
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡