የአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን ያዘጋጀው በኢትዮጵያ እግርኳስ የሚታየውን የሊግ ውድድር የአደረጃጀት ችግሮች በመለየትና የመፍትሔ ሀሳቦች በማስቀመጥ ላይ ያተኮረ ጥናት በዕለተ ሰኞ በሸራተን አዲስ ሆቴል ሲቀርብ የመግባቢያ ሰነድም ተፈርሟል።
የአአ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ተወካይ፣ አአ የስፖርት ኮሚሽን ኃላፊዎች፣ የአአ እግርኳስ ፌዴሬሽን የስራ አስፈፃሚ አባላት እንዲሁም የ22 ክለቦች ፕሬዝዳንቶች በተገኙበት ነበር የስምምነት ፊርማ የተከናወነው፤ እንዲሁም ጥናታዊ ፅሁፍ ለውይይት የቀረበው።
አቶ ኃይለኢየሱስ ፍስኃ (የአአ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት) የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ካደረጉ በኋላ መድረኩን የተረከቡት አቶ ገዛኸኝ ወልዴ ጥናት አቅርበዋል። ጥናቱ በዋናነት ያተኮረው የሊግ ውድድር አደረጃጀቶች ችግሮች ምን እንደሆኑ ነው። ለጥናቱ የሚሆኑ መረጃዎችን (ሰነዶችን) በማሰባሰብ እና መጠይቆችን በመበተን ለጥናቱ የሚሆኑ ግብዓቶች እንዳገኙ ተናግረው ” የክለቦች የሊግ ውድድር በዋናነት የሚጠቅመው የአንድን ሀገር እግርኳስ ለማሳደግ መሆን እንዳለበት ያስቀምጣል።” ያሉት ጥናት አቅራቢው በዚህም ምክንያት ” አሁን በኢትዮጵያ እየሰራ ያለው የሊግ አደረጃጀት በርካታ ውስብስብ ችግሮች እንዳሉበት የጥናቱ ድምዳሜ ያሳያል።” ሲሉ በዝርዝር ተናግረዋል።
አቶ ገዛኸኝ ባቀረቡት ጥናት አሁን ያለው የሊግ አደረጃጀት በፋይናስ ረገድ ክለቦች ላይ እያሳደረ ያለው ተፅእኖ ምንድነው የሚለውን በቀዳሚነት አቅርበዋል።
” የኢትዮጵያ የሊግ ውድድር በሦስት እርከን የተከፈለ ነው። ፕሪምየር ሊግ፣ ከፍተኛ ሊግ እና አንደኛ ሊግ ይሰኛል። በዚህ ውድድር ውስጥ በአጠቃላይ በተጠናው ጥናት መሠረት ሁለት ነጥብ ሁለት ቢልየን ብር በየዓመቱ ወጪ ይደረግበታል። ከዚህ ውስጥ 95% ከመንግስት ካዝና ወጪ የሚሸፈን ነው። ምክንያቱም አብዛኛዎቹ ክለቦች የከተማ ቡድኖች በመሆናቸው ነው።
” ይህ ገንዘብ በዋናነት ወጪ እያደረገ ያለው ለተጫዋቾች ወርኃዊ ደሞዝ ፣ ለምግብ እና መኝታ ፣ ለተዟዙሮ ለመጫወት ለትራንስፖርት የሚውል ነው። በዋናነት ተዟዙሮ መጫወት በሁሉም እርከኖች ለትራንስፖርት ብቻ ግማሽ ቢልየን (አራት መቶ ዘጠና ሚልየን ስምንት መቶ ሺህ) ብር በዓመት ወጪ ይደረጋል። ይህ ሁሉ ወጪ ወጥቶ አንድ በፕሪምየር ሊግ ውድድር የሚሳተፍ ቡድን አሸናፊ ሆኖ ካጠናቀቀ 150 ሺህ ብር የገንዘብ ሽልማት ያገኛል። ስለዚህ ወጪው እና ገቢው የማይመጣጠን የገንዘብ ቀውስ ያለበት የሊግ አደረጃጀት እንደሚገኝ ማሳያ ነው። የፊፋ የክለቦች ላይሰንስ ላይ ሲያስቀምጥ በምንም መንገድ የአንድ ክለብ ወጪ እና ገቢው መበላለጥ እንደሌለበት ይደነግጋል። በኢትዮጵያ ያለው ነባራዊ ሁኔታ ይሄን የሚያሳይ አይደለም። በአጠቃላይ የኢትዮጵያ እግርኳስ የሊግ አደረጃጀት ከፋይናንስ አንፃር ሲታይ ከፍተኛ ችግር ያለበት ፣ የመንግስትን ገንዘብ ጥቅም በሌለው መንገድ የሚያስወጣ እና በሚወጣው ገንዘብ ልክ የእግርኳስ ልማት ላይ ምንም ሳይሰራ ቆይቷል። ይህን የፋይናስ ዝውውሩን አስመልክቶ ያለውን የሊግ ፎርማት መቀጠል አለበት ብለው የሚከራከሩ ሳየይር የፋይናሻል ኪሳራ እንዳለባቸው በተበተነው መጠይቅ ላይ ሲናገሩ ማስተዋል ተችሏል።”
ጥናቱ በሁለተኝነት የዳሰሰው የአሁን ያለው የሊግ ውድድር የመዋቅር አደረጃጀት ምን ይመስላል የሚለው ነው።
” የሊግ አደረጃጀቱ ከዓለም አቀፍ የሊግ ውድድር አደረጃጀት አንፃር በትንሹ ሟሟላት የሚገባን አሏሟላም። የሊግ አስተዳደር መመርያ የለውም፣ የክለቦች ተሳትፎ የለበትም፣ ተቋማዊ ቅርፅ የለውም፣ በስራ አስፈፃሚው የሚመራው የሊግ ኮሚቴ አደረጃጀት የሚመራበት እና የሚሰራበት የውስጥ ደንብ እና የስራ ዝርዝር የለውም፣ የሊግ ኮሚቴው በክለቦች ተቀባይነት ያገኘ አደረጃጀት የለውም፣ የኮሚቴ አባላት ጥንቅር (ኃላፊነታቸው) በዝርዝር አይታወቅም። የፌዴሬሽኑ ዳይሬክቶሬት ዳሬክተር እና የሊግ ኮሚቴው ምንድነው የሚሰራው የሚል በመሐከላቸው በግልፅ የተቀመጠ የስራ ዝርዝር ድልድይ የላቸውም ። በአጠቃላይ የሊግ አደረጃጀቱ በአማተር የተመራ ያለ እና በልምድ የሚሰሩ ያሉ ግለሰቦች ጥገኛ የሆነ እግርኳሱን መመራት በሚያስችል ቁመና ላይ የማይገኝ የሊግ አደረጃጀት እንዳለን የሚሳይ ጥናት ነው። ” ሲሉ ገልፀዋል።
በሦስተኝነት በጥናቱ የተዳሰሰው የዓለም አቀፍ መርሆችን የጣሰ ነው የሚል ነው። ” ፊፋ በ2016 ባቀረበው የሪፎርም ጥናት ላይ ሁሉም አባል ሀገራት በመተዳደርያ ደንባቸው እንዲሁም በሊግ አስተዳደር ስርዓታቸው ላይ እነዚህን ማስገባት እንዳለባቸው ይገልፃል። የመጀመርያው ከፖለቲካ አመለካከት እና ከዕምነት ገለልተኛ መሆን እንዳለበት ያስቀምጣል። አሁን ያለው የሀገራችን የእግርኳስ ስንመለከት የፖለቲካ አስተሳሰብ የተጫነው የሊግ አደረጃጀት እየሆነ መጥቷል። ይህ ዓለም አቀፍ የእግርኳስ መርህን የጣሰ መሆኑን ያሳያል።”
በአራተኝነት የተቀመጠው የፍትህ አካላት ሚና ነው። ” እነዚህ አካላት ማለትም ዲሲፕሊን እና ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ገለልተኛ ሆነው መቋቋም እንዳለባቸው የፊፋ ጥናት ያሳያል። ይህም ብቻ ሳይሆን የፍትህ አካላት የሚዋቀሩት በጠቅላላ ጉባኤ አባላት እንደሆነ እና ተጠሪነታቸውም ለጠቅላላ ጉባዔው አባላት መሆን እንዳለበት የፊፋ ህግ ያስቀምጣል። ወደ እኛ ስንመጣ የፍትህ አካላት የሚደራጁት በስራ አስፈፃሚ አካላት መሆኑ ፍፁም ስህተት መሆኑን ያሳያል። እነዚህ የፍትህ አካላት ተጠሪነታቸው ለስራ አስፈፃሚ መሆኑ ከዓለም አቀፉ የእግርኳስ መርህ ያፈነገጠ የሊግ አደረጃጀት እንዳለ ማሳያ ነው።”
በአቶ ገዛከኝ ማብራርያ በአምስተኛ ላይ የተቀመጠው የጨዋታ መርሆች ናቸው። “የጨዋታ ህግ የታማኝነት ፣ የአንድነት ፣ የስፖርተኝነት እና ተገቢ የሆነ አጨዋወት መርህን ማክበር የሚለው ነው። አሁን ባለው የሊግ አደረጃጀት ወይም ተዟዙሮ በመጫወት ፎርማት ውስጥ ተገቢ የሆነ አጨዋወት (ፌር ፕሌይ) ማግኘት አዳጋች ሆኗል። በሜዳህ ታሸንፋለህ ሆኖም ከሜዳ ውጭ ማሸነፍ የማይታሰብ ሆኖ መጥቷል። ይህ ደግሞ ማሸነፍ በአቅም መሆኑ ቀርቷል። ይህ የሚያሳየው ማሸነፍ በአካባቢ እየሆነ መምጣቱን ማሳያ ነው። በአጠቃላይ የእግርኳስን መርህ ያልተከተለ እግርኳሳዊ ውድድሮች የማይደረጉበት የእግርኳስ ውድድርን የማንነት እና የብሔር መፎካከርያ መድረክ ያደረገ የሊግ አደረጃጀት ሆኗል ማለት ነው።”
ሌላው በጥናቱ የቀረበው አሁን በስራ ላይ ያለው የሊግ አደረጃጀት ከክልሎች እና ከከተማ አስተዳደሮች ተሳትፎ አንፃር ሲመዘን ምን ይመስላል በሚል ነው።
” ሁሉን ውድድር የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጠቅልሎ የያዘ በመሆኑ የአንዳንድ ክልሎች አቅም (ታለንት) ያላቸው ተጫዋቾች የሚያሳዩበት እድል እንዳይኖራቸው አድርጓል። የክልሎችን የውስጥ ውድድር አዳክሟል። ለምሳሌ ይህ ፎርማት ውድድር ከመጀመሩ በፊት ኦሮሚያ ላይ 16 ጠንካራ ቡድኖች ነበሩ። በደቡብ እና በአዲስ አበባ ጠንካራ ቡድኖች በተመሳሳይ ነበሩ። ወደ ኢትዮጵያ ሻምፒዮና ሲመጡ እልህ አስጨራሽ ትግል ያደርጉ እንደነበረ መዛግብት ይናገራሉ። አሁን ያለው የሊግ አደረጃጀት እነዚህን ቡድኖች ገሏቸዋል፤ አጥፍቶቸዋል። ለዚህም ማሳያ ባለፉት ዓመታት 16 ቡድኖች የመፍረስ ዕጣ ውስጥ ገብተዋል። ለምሳሌ ፐልፕና ወረቀት ፣ ጉና ፣ ትራንስ ፣ ሀረር ቢራ ፣ ድሬደዋ ጨርቃጨርቅ ፣ ፊንጫ ስኳር ፣ አየር ኃይል እና ሙገር ሲሚንቶ… ቡድኖች ከፕሪምየር ሊጉ እንደወረዱ የመፍረስ እድላቸው ሰፊ እንደሆነ ጥናቶች ያሳያሉ። በአጠቃላይ የክልሎቹ የውስጥ ውድድሮች መዳከም አቅም ያላቸውን ተጫዋቾች እንዳይወጡ ያደረገ ይሉቅንም ክለቦች በጥቂት ተጫዋቾች እንዲሽከረከሩ ያድገ እና የሚወጣው በሚልየን የሚቆጠር ገንዘብ ለብክነት የተዳረገበት የሊግ አደረጃጀት እንዳለን ጥናቱ ያሳያል። ”
በተጨማሪ ጥናቱን ያቀረቡት አቶ ገዛኸኝ ከፀጥታ እና ከደህንነት አኳያ የአሁን ያለው የሊግ አደረጃጀት ያለበትን ሁኔታ አብራርተዋል።
” እግርኳሱ የሰላም የወንድማማችነት መንፈስ የተላበሰ መሆኑ ቀርቶ የሀገር ስጋት እየሆነ መጥቷል። አሁን ያለው የስፖርታዊ ጨዋነት አይደለም። አንዳንድ ቦታ እንዳየነው በሜዳው አሸንፎ እንኳን በሰላም የማትወጣባቸው ሁኔታዎች እየተፈጠሩ ነው። ይህንን ችግር ለመቆጣጠር ሲባል የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ እየተባለ ስያሜው በገለልተኛ ሜዳ የሚደረጉ ጨዋታዎች እየተበራከቱ መጥተዋል። ለእነዚህ የፀጥታ ችግሮች መፈጠር ምክንያቱ የብሔር ክለቦች መብዛት እና የክለቦቹ ስያሜዎች እና አርማዎቹ ብሔር ተኮር መሆናቸው ነው።
ሌላው የእግርኳስ ሙስና የጨዋታ ውጤት ማጭበርበር በስፋት ይታያሉ። ዳኛ መያዝ ፣ የጥቅም ግኑኝነት ሠንሰለት ፕሪምየር ሊግ ለመግባት እና ላለመውረድ እንዲሁም አሸናፊ ሆኖ ለማጠናቀቅ በስፋት የእግርኳስ ሙስና እየተንፀባራቅ መሆኑን ጥናቱ አረጋግጧል።” ብለዋል።
በተጨማሪም “በእግርኳስ መሠረተ ልማት ላይ ክለቦች ትኩረት ከማድረግ ይልቅ የሚያገኙትን ገንዘብ ለውድድር ብቻ እንዲያወጡ አድርጓል። በዚህ ምክንያት የታዳጊዎች አካዳሚ ፣ የእግርኳስ መሠረተ ልማት ላይ እንዳያተኩሩ አድርጓቸዋል። ይህም በብሔራዊ ቡድን ላይ ያሳደረውን ተፅእኖ (ውድቀት) አስከትሏል።” በሚል በቁጥራዊ መረጃዎች ቀርቧል።
በአጠቃላይ ይህ የሊግ አደረጃጀት ብዙ ክፍተቶች ያለበት እና አዋጭ ባለመሆኑ አማራጭ የሊግ አደረጃጀት ማቅረብ ያስፈልገል። በማለት ጠቃሚ የሆነ ምክረ ሀሳብ በጥናቱ መሠረት ለጉባዔተኛው ቀርቧል። በዚህም መሠረት ተዟዙሮ መጫወትን በማስቀረት እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉም የውስጥ ውድድሩን አጠናቆ የኢትዮጵያ ሻምፒዮን ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን በማቅረብ ጥናታዊ ፁሁፋቸውን አጠናቀዋል።
በመቀጠል በቀረበው ጥናት ውይይት ከመደረጉ በፊት የአአ አስተዳደር የከንቲባው ተወካይ አቶ ኃይለሰማዕት መርሐጥበብ እንደ አንድ የስፖርት ሳይንስ ባለሙያ ጥናቶች ጠቀሜታቸውን ገልፀው ” የኢትዮጵያ ስፖርት አሁን መዳን አለበት። ለዚህም የአዲስ አበባ ቡድኖች ምሳሌ መሆን አለባቹችሁ። ይህ ጥናትን መቶ በመቶ እስማማበታለው። መፍትሄ ማበጀት ካልቻልን በእኛ ሀገር ባለው የገንዘብ አወጣጥ ስርዓት ብዙ ብክነቶች ይመጣሉ። እግርኳሳችን የፖለቲካ ማንፀባረቂያ ሆኗል። ይህ መድረክ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡናን ከክለብ ባላንጣነት ወደ ኅብረት እና አንድነት ያመጣ መሆኑ ለአዲስ አበባ እና ለእግርኳሱ ትንሣኤ ነው።” ብለዋል።
በቀረበው ጥናት ዙርያ ተጨማሪ ሰፊ ውይይት ከተደረገ በኋላ በቀጣይ ምን መደረግ አለበት በሚለው ዙርያ የተለያዩ ሀሳቦች ቀርበዋል። በአንድ ወገን አብዛኛዎቹ የራሳችን ውድድር የምናደርግበት የሊግ ውድድር ይኑረን ሲሉ የኢትዮጵያ መድን እና ፌደራል ፖሊስ ተወካዮች ” በሀሳቡ ሙሉ ለሙሉ ተስማምተናል። ሆኖም ለአለቆቻችን አሳውቀን እንፈርማለን።” ያሉ ሲሆን አቶ አብነት ገብረመስቀል እና መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ የመጨረሻ ጠንከር ያሉ መልክቶች አስተላልፈዋል።
አቶ አብነት ” የአዲስ አበባ ክለቦች እስከ ዛሬ ድረስ በየክልሉ ስንሄድ ያልደረሰብን ዛቻ እና ድብደባ የለም። በአሁን ሰዓት የአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን ከእኛ ጎን የቆመበት ጊዜ ስለሆነ እኛ አንድ መሆን አለብን። የእኛ አንድ አለመሆን ነው ምስቅልቅሉ የወጣ ስራ አስፈፃሚ መርጠን ዋጋ እየከፈለን ያለነው። ስለዚህ ይህ አሁን ያለው የውድድር ፎርማት ይቀየር። እንደ አዲስ አበባ አንድ ሆነን በራሳችን ውድድር እናካሂድ። በዚህ ምክንያት ጉሮሯቸው የሚዘጋ ጥቅማቸው የሚቀርባቸው ግለሰቦች የተለያየ ስም ሊሰጡን ይችላሉ። እኛ የፖለቲካ የብሔር እና ቡድኖች አይደለንም። ለሀገራችን ሰላም የሚጠቅመውን ነው እያሰብን ያለነው።” ብለዋል።
መቶ አለቃ ፍቃደ በበኩላቸው ” ባለፉት ጊዜያት የተለያዩ ውይይቶችን ስናደርግ ቆይተናል። አሁን ወሳኝ ጊዜ ላይ ደርሰናል። እስከዛሬ በነበረው የሊግ ፎርማት የኢትዮጵያ እግርኳስ ውስጥ ከፍተኛ ሀብት ያከበቱ ግለሰቦች ምን ዓይነት ሀብት እንዳፈሩ ከነመረጃው በጥናት የምናቀርበው ይሆናል። እነዚህ ግለሰቦች የራሳችንን ውድድር ስናካሄድ ከፍተኛ ጥቅም የሚያስቀር በመሆኑ እኛን ለማዳከም በየቦታው እየተንቀሳቀሱ ነው። መዘግየታችን በጣም ነው የጎዳን። ቡናና ጊዮርጊስ ማሸነፍ ስላልቻሉ ነው ፎርማቱ ይቀየር የሚሉት ይሉናል። አሁን ደግሞ የልብ ልብ ተሰምቷቸው ቡናና ጊዮርጊስ የራሳቸውን ውድድር ብቻቸውን ያድርጉ እያሉ ይሳለቁብናል። አሁን ጉዳዩ የኢትዮጵያ ቡና እና የቅዱስ ጊዮርጊስ ብቻ አይደለም የኢትዮጵያን እግርኳስ ከውድቀት፣ ከሞት ለማዳን ነው። ከዚህ በኃላ ለአንድ ቀን ማደር አንችልም። ይህን የመግቢያቢያ ሰነድ መፈረም አለብን ። ” ብለዋል።
በመጨረሻም ከፌደራል ፖሊስ ክለብ በቀር በስብሰባው ላይ የተገኙ ክለቦች ለእግርኳሱ ዕድገትም ሆነ አላግባብ የሚወጡ የመንግስት የገንዘብ ወጪን ለማስቀረት በሚል ከ2012 ጀምሮ በአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን ስር በመሆን ለመወዳደር በጋራ ተስማምተው ተፈራርመዋል።
ስምምነታቸውንም የአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን ለሚመለከተው አካላት በሙሉ እንዲያደርስ ወስነው ጉባዔው ተጠናቋል።
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡