የውድድር ዘመኑ አጋማሽ ላይ ከአሰልጣኝ ሥዩም ከበደ ጋር ተለያይቶ በአሰልጣኝ በለጠ ገ/ኪዳን ጊዜያዊ አሰልጣኝነት ሲመራ የቆየው መከላከያ በመጨረሻም የክለቡ የስራ አመራር ቦርድ ውይይት ካደረገ በኋላ ዘላለም ሽፈራውን ዋና አሰልጣኝ አድርጎ ሾሟል።
አሰልጣኝ ዘላለም በክለቡ ፅህፈት ቤት በመገኘት ለአንድ ዓመት የሚያቆያቸውን ፊርማ ያኖሩ ሲሆን በቀጣይ ቀናት ረዳቶቻቸውን ያሳውቃሉ ተብሎ ሲጠበቅ ክለቡንም ለማጠናከር ወደ ሥራ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።
አሰልጣኝ ዘላለም ያለፉትን ወራት ከደቡብ ፖሊስ ጋር ከተለያዩ በኋላ ከማሰልጠን የራቁ ሲሆን ከዚህ ቀደም በአዳማ ከተማ፣ ደደቢት፣ ሀዋሳ ከተማ፣ ሲዳማ ቡና፣ ድሬዳዋ ከነማ ፣ወልድያ እና ደቡብ ደቡብ ፖሊስ እንዲሁም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ረዳት) ማሰልጠናቸው ይታወቃል።
ሁለት ዋንጫ በማንሳት የውድድር ዓመቱን በስኬት የጀመረው መከላከያ ዓመቱን ወደ ከፍተኛ ሊግ በመውረድ ማጠናቀቁ ይታወቃል። ሆኖም “ወደ ታችኛው ሊግ የወረድኩበት መንገድ እግርኳሳዊ ባልሆነ ምክንያት ነው።” በማለት ለፌዴሬሽኑ ቅሬታውን አስገብቶ ምላሽ እየተጠባበቀ ይገኛል።
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡