ቻምፒየንስ ሊግ | መቐለ 70 እንደርታ ወደ ማላቦ አቅንቷል

መቐለ 70 እንደርታዎች በታሪካቸው ለመጀመርያ ጊዜ የካፍ ቻምፒየንስ ሊግ ጨዋታ ለማድረግ ወደ ኢኳቶርያል ጊኒ ማላቦ ጉዞ ጀምረዋል።

የተጠናቀቀው የውድድር ዓመት የፕሪምየር ሊግ አሸናፊ መቐለ 70 እንደርታዎች ቅዳሜ በማላቦ ከካኖ ስፖርትስ አካዳሚ ጋር ላላቸው ጨዋታ ዛሬ ወደ ስፍራው አምርተዋል። ለውድድሩ ቀደም ብለው ቅድመ ዝግጅት የጀመሩት መቐለዎች የዝውውር መስኮቱ ቀደም ብለው ገብተው ከበርካታ ተጫዋቾች ጋር ተስማምተው የነበረ ቢሆንም ብዙም ሳይቆዩ ከሁለት ተጫዋቾች ጋር ተለያይተዋል።

ብዙም ለውጥ ሳያደርጉ በአመዛኙ የባለፈው ዓመት ስብስባቸው ይዘው ወደ ማላቦ ያቀኑት ቻምፒዮኖቹ ከአዲስ ፈራሚዎቻቸው መካከል ታፈሰ ሰርካ እና ኤፍሬም አሻሞን ይዘው ወደ ስፍራው ሲያቀኑ አልሃሰን ካሉሻ በጉዳት ወደ አብሮ አልተጓዘም።

በወጣቶች የተገነባ ቡድን ያላቸው ባለሜዳዎቹ ካኖ ስፖርትስ አካዳሚ ክርስትያን የተባለ ተጫዋቻቸው በጉዳት የመሰለፉ ነገር አጠራጣሪ ነው። ቡድናቸው ከሁለት የሶኦ ቶሜ እና ፕሪንስፔ ዜግነት ያላቸው ተጫዋቾች ውጭ በሃገራቸው ተጫዋቾች የተገነባ ሲሆን ለዚህ ውድድር ይረዳቸው ዘንድ ጆርገ ሞሴራ፣ ኤድዋርዶ አስካኦ (ዲንሆ) እና ኔቬስ ኳሬስማ (ዲልሰን) የተባሉ ተጫዋቾች አስፈርመዋል።

በፓብሎ ቦያስ ደሳምፓካ ስቴድየም የሚካሄደው ጨዋታው ቅዳሜ 11፡00 ላይ ይደረጋል።

ወደ ስፍራው ያቀኑ ተጫዋቾች ዝርዝር

ግብ ጠባቂዎች፡ ፍሊፕ ኦቮኖ፣ ሶፎንያስ ሰይፈ

ተከላካዮች፡ አሌክስ ተሰማ፣ አሚን ነስሩ፣ ታፈሰ ሰርካ፣ አንተነህ ገ/ክርስቶስ፣ ኄኖክ ኢሳይያስ፣ ሥዩም ተስፋዬ

አማካዮች፡ ሚካኤል ደስታ (አምበል)፣ ጋብርኤል አሕመድ፣ ሐይደር ሸረፋ፣ ዮናስ ገረመው፣ ሙሉጌታ ወ/ጊዮርጊስ፣ ሳሙኤል ሳሊሶ፣ ኤፍሬም አሻሞ፣ ያሬድ ከበደ

አጥቂዎች፡ ያሬድ ብርሃኑ፣ ኦሴይ ማውሊ፣ አማኑኤል ገ/ሚካኤል


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡