ሀዋሳ ከተማ ወጣቱን አጥቂ የክለቡ ከፍተኛ ተከፋይ አድርጓል

በቅርቡ ከወጣት ቡድን ያደገው አጥቂ መስፍን ታፈሰ በዋናው ቡድን ባሳየው ብቃት የክለቡ ከፍተኛ ተከፋይ በመሆን ውሉን ማራዘሙን አሰልጣኙ ለሶከር ኢትዮጵያ ገለፁ።

መስፍን ታፈሰ ክለቡ በመጋቢት ወር መጨረሻ ከ20 አመት በታች ቡድኑ ካሳደገው በኋላ በፍጥነት በመላመድ በሁሉም ውድድሮች ስምንት ጎሎችን ማስቆጠር የቻለ ሲሆን ይህ አቋሙም ለብሔራዊ ቡድኑ ጥሪ እንዲደርሰው ምክንያት ሆኗል። በቻን ማጣርያ ኢትዮጵያ ጅቡቲን 4-3 ባሸነፈቸችበት ጨዋታ ተቀይሮ በመግባት የመጀመርያ ጨዋታውን አከናውኖም የማሸነፍያ ጎል ማስቆጠሩ ይታወሳል።

አሰልጣኝ አዲሴ ካሳ በተለይ ለሶከር ኢትዮጵያ እንደገለፁት ተጫዋቹ የአንድ ዓመት ኮንትራት ቢቀረውም አሁን የሚከፈለው ዝቅተኛ ወርሀዊ ደሞዝ በከፍተኛ ሁኔታ ተሻሽሎ የክለቡ ከፍተኛ ተከፋይ በማድረግ ለተጨማሪ ሁለት ዓመታት ውሉ ተራዝሟል። “ከአሁን በኋላ እኛ ብቻ ሳንሆን ሁሉም ክለቦች በወጣቶች ላይ መስራት አለብን። የዚህ ወጣት ተጫዋች አመጣጥም ይህንን ያሳየናል። እኔም ከተጫዋቹ ባየሁት ነገር ተነስቼ ለሌሎችም ዕድሉን ለመስጠት ተዘጋጅቻለሁ። ” ሲሉም አክለዋል።

በስብስቡ ውስጥ ከግማሽ በላይ ከወጣት ቡድን ያደጉ ተጫዋቾችን የያዘው ሀዋሳ ከተማ በቅርቡ ከተስፋ ቡድን ተጨማሪ የሚያድጉ ተጫዋቾች እንደሚኖሩ እና በቅርቡ ላደጉት ግብ ጠባቂው ምንተስኖን ጊንቦ እና ምንተስኖት እንድሪያስም የተሻሻለ ውል እንደሚቀርብላቸው አሰልጣኙ ገልፀዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡