የ2011 የኢትዮጵያ ክልል እና ከተማ አስተዳደር ክለቦች ሻምፒዮና ከሐምሌ 14–ነሐሴ 2 ድረስ ያለፉትን አስራ አምስት ቀናት በአዳማ በብዙ አስገራሚ ትዕይቶች ታጅቦ ሲካሄድ ቆይቶ በሀሳሳ ከተማ አሸናፊነት ተጠናቋል።
03:00 ላይ ሾኔ ከተማን ከኣብዲ ሱሉልታ ያገናኘውን የ3ኛ ደረጃ ጨዋታ በፍፁም የበላይነት ሾኔ ከተማ 5-1 አሸንፎ ሦስተኛ ደረጃ በመያዝ አጠናቋል። በመከላከያ በመለያ ምት ተሸንፎ የፍፃሜ ዋንጫ አይድረስ እንጂ እጅግ የተሟላ ቡድን ሆኖ በውድድሩ የቀረበው ሾኔ ከተማ በኣብዲ ሱሉልታ ላይ ፍፀም የበላይነት በመውሰድ ነው አሸንፎ መውጣት የቻለው። በመስመር አጨዋወታቸው ጥቃት የሚሰነዝሩት ሾኔዎች ኃይሉ ሽኩር ባስቆጠራት ጎል መምራት ሲጀምሩ ብዙም ሳይቆዩ በጥሩ መንገድ ወደፊት በመሄድ አቤል ዮሐንስ ሁለተኛ ጎል አስቆጥሮ ወደ እረፍት አምርተዋል።
በሁለተኛው የጨዋታ አጋማሽ ኣብዲ ሱሉልታዎች በተሻለ ለመንቀሳቀስ ቢሞክሩም የተለየ ነገር ማሳየት ባለመቻላቸው ውጤቱን ለመቀልበስ ሲቸገሩ ተስተውሏል። ይሉቁንም ሾኔዎች ኃይሉ ሽኩር ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ ሦስተኛ ጎል አስቆጥሮ የጎል መጠናቸውን ወደ ሦስት ከፍ አድርገዋል።
በጨዋታው እጅግ አስገራሚ ክስተት በ71ኛው ደቂቃ ተከስቷል። በልምምድ ላይ እንደሆነ መገመት በሚያስችል ሁኔታ አንድ ሄሊኮፍተር ጨዋታውን በማቋረጥ ካረፈች በኋላ በድጋሚ ተነስታ መብረሯ በዕለቱ ጨዋታውን ለመከታተል በስታዲየም የተገኙትን የስፖርት ቤተሰብ ያስገረመ ሆኖ አልፏል።
ጨዋታው ከተቋረጠበት ቀጥሎ ሲካሄድ በውድድሩ ላይ ልምድ ካላቸው ተጫዋቾች መካከል የሚመደበው እና ለሾኔ ጥንካሬ ተጠቃሽ የሆነው ደረጄ ጥላሁን አራተኛ ጎል አስቆጥሯል። በኣብዲ ሱሉልታ በኩል መዳከም በታየበት በዚህ ጨዋታ ለቡድኑ ብቸኛ ጎል ሐብታሙ ታደሰ አስቆጥሯል። በሾኔዎች ሌላው ተቀይሮ የገባው ወንድማገኘው ዓየሁ አምስተኛ የመጨረሻ ጎል አስቆጥሮ ጨዋታው በሾኔ የበላይነት 5-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። ሾኔ ከተማም ውድድሩን ሦስተኛ ደረጃ በመያዝ አጠናቋል።
08:00 የመከላከያና የሀሳሳ ከተማ የፍፃሜ ዋንጫ ጨዋታ በደማቅ ሥነ ስርዓት ተካሂዶ ሀሳሳ ከተማ ከእረፍት መልስ ባስቆጠራት ብቸኛ ጎል 1-0 በማሸነፍ የውድድሩ አሸናፊ በመሆን አጠናቋል።
የፌዴሬሽኑ ፕሬዝደንት አቶ ኢሳይያስ ጂራና የሁለቱም ክለብ አመራሮች በክብር እንግድነት በተገኙበት፣ የመከላከያ ሠራዊት የማርሽ ባንድ ለውድድሩ መዝግያ ድምቀት የሆኑ የተለያዩ ዜማዎች ባሰማበት በዚህ የፍፃሜ ጨዋታ በተደጋጋሚ ወደ ጎል የሚደረስ ሙከራዎች ባይኖሩበትም ጥሩ ፉክክር አስመልክቶን ጨዋታው ተጠናቋል። 11ኛው ደቂቃ ላይ በሀሳሳ በኩል መላኩ ክፍሌ ከቀኝ መስመር ወደ ሳጥኑ ሰብሮ በመግባት ከእርሱ በተሻለ ነፃ አቋቋም ለሚገኘው ተከተል አለልኝ ማቀበል ሲችል ራሱ ለመጠቀም በማሰቡ የመከላከያው ግብጠባቂ አዲስዓለም ወደ ውጭ ያወጣበት የጨዋታው የመጀመርያ ሙከራ ነበር። ከጨዋታ ውጭ የሆኑ አቋቋሞች በሁለቱም ቡድኖች በኩል በመብዛቱ የፍፃሜ ጨዋታውን እያቀዘቀዘው ቀጥሎ 29ኛው ደቂቃ በመከላከያ በኩል ከሳጥን ውጭ በጥሩ ሁኔታ ዮናስ ኃ/ማርያም አክርሮ የመታው ኳስ የግቡ አግዳሚ የመለሰበት በመከላከያ በኩል የሚያስቆጭ በጨዋታው ላይ የታየ ብቸኛ የጎል ሙከራ ነበር።
ከእረፍት መልስ መከላከያዎች ሲቀዛቀዙ ሀሳሳዎች በእንቅስቃሴ ብዙም ብልጫ ባይኖራቸውም በመጫወት ፍላጎት የተሻሉ ነበሩ። በ60ኛው ደቂቃ ከመስመር የተሻገረውን ኳስ በመከላከያ ተከላካዮች ተደራርቦ ከጎሉ ሦስት ሜትር ርቀት የነበረው ተካልኝ አለልኝ አግኝቶ በጥሩ አጨራረስ ወደ ጎልነት በመቀየር የሀሳሳን ጎል አስቆጥሯል። ከጎሉ መቆጠር በኃላ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ተነቃቅተው ጫና የፈጠሩት መከላከያዎች 75ኛው ደቂቃ አብዶም ኃ/ሥላሴ ከግራ መስመር ተከላካዮችን በማለፍ ያሻማውን ኳስ የመከላከያ አጥቂዎች እርስ በእርስ ሲገባበዙ ኳሱን ሳይጠቀሙበት የቀረው ዕድል የሚያስቆጭ ነበር። በመልሶ ማጥቃት ከአንዴም ሁለቴ የጎል መጠናቸውን ከፍ በማድረግ የሚችሉበትን አጋጣሚዎች ሳይጠቀሙ የቀሩ ቢሆንም በመጨረሻም ጨዋታው ሀሳሳ ከተማዎች 1-0 በሆነ ውጤት አሸንፈው የውድድሩ አሸናፊነት ሆነዋል።
በመጨረሻም የኮከቦች ሽልማት ሲካሄድ የሚከተሉት ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡-
ኮከብ ጎል አስቆጣሪ – ያሬድ ሽመልስ በ6 ጎል ከደጋን ከተማ
ኮከብ ተጫዋች – ዳንኤል ኃ/ማርያም ከመከላከያ
ኮከብ ግብ ጠባቂ – አብዱረዛቅ ተማም ከ ሀሳሳ ከተማ
ኮከብ አሰልጣኝ – ግርማ ሰዒድ ከ ሀሳሳ ከተማ
የስፖርታዊ ጨዋነት ተሸላሚ – መከላከያ
ምስጉን ዳኞች – አህመድ ሲራጅ ፣ ተከተል በቀለ፣ ሸረፈዲን አልፈኪ እና ሰለሞን አሸብር
ወደ አንደኛ ሊግ ያደጉ ስምንት ቡድኖች፡ ሾኔ ከተማ፣ ሀሳሳ ከተማ፣ ፈራውን ከተማ፣ሐውዜን ከተማ፣ ኤጀሬ ከተማ፣ መከላከያ፣ ኣብዲ ሱሉልታ እና ደጋን ከተማ
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡