በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት ከወራጅነት ለጥቂት ማምለጥ የቻለው ስሑል ሽረ ሦስት ተጫዋቾችን ወደ ቡድኑ መቀላቀሉን ሲያስታውቅ የሁለት ተጫዋቾችን ውል አድሷል።
የመጀመሪያው ፈራሚ በኢትዮጵያ ቡና ያለፉትን ሁለት ዓመታት ያሳለፈው ወንድወሰን አሸናፊ ነው። ግብ ጠባቂው ከዚህ ቀደም በሙገር ሲሚንቶ እና ወላይታ ድቻ የተጫወተ ሲሆን ዘንድሮ ኢስማኤል ዋቴንጋ ባልተሰለፈባቸው ጨዋታዎች ላይ የቡናን ጎል ጠብቋል።
ሌላው የሽረ አዲስ ፈራሚ በረከት ተሰማ ነው። የተከላካይ መስመር ተጫዋቹ ኤሌክትሪክን ለቆ ወልዋሎን በ2010 ከተቀላቀለ በኋላ በተለይ በመጀመርያው ዓመት ጥሩ አቋም ከማሳየቱ በተጨማሪ ቡድኑንም በአምበልነት መምራት ችሎ ነበር።
አዳም ማሳላቺ ሦስተኛው ፈራሚ ነው። ጋናዊው የመስመር ተከላካይ ስፍራ ተጫዋች ከዚህ ቀደም በ2010 ወደ ለመቐለ ፈርሞ የነበረ ቢሆንም የውድድር ዓመቱ ሳይጀመር ነበር በጉዳት ምክንያት ከቡድኑ ጋር የተለያየው።
ሦስቱንም ተጫዋቾች በአንድ ዓመት የውል ስምምነት ለማስፈረም የተስማማው ሽረ የነባሮችን ውል ለማደስም እየተንቀሳቀሰ የሚገኝ ሲሆን በዓመቱ መጀመርያ ቡድኑን የተቀላቀሉት አብዱሰላም ዓማን እና ዲሜጥሮስ ወልደሥላሴ ውላቸውን ለተጨማሪ ዓመት አራዝመዋል።
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡