” ቡድናችን የቻምፒዮንነት እና የማሸነፍ መንፈስ ላይ ነው ያለው” ሚካኤል ደስታ

መቐለ 70 እንደርታ በታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜ የሚያደርገውን የቻምፒየንስ ሊግ ጨዋታ ነገ 12፡00 ላይ ከኢኳቶርያል ጊኒው ካኖ ስፖርት አካዳሚ ጋር ያከናውናል። ቡድኑን በአምበልነት እየመራ ወደ ጨዋታው ይገባል ተብሎ የሚጠበቀው አማካዩ ሚካኤል ደስታም ስለ ዝግጅታቸው እና ተያያዥ ጉዳዮች ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር አጭር ቆይታ አድርጓል።

ለውድድሩ እያደረጋችሁት ቅድመ ዝግጅት ምን ይመስላል?

ለውድድሩ ያደረግነው ዝግጅት መልካም ነው። በውድድሩ ልምድ ያለው አሰልጣኝ ነው ያለን፤ በነበሩብን ክፍተቶችም አዳዲስ ተጫዋቾች ጨምረናል። ይሄንን ጨዋታ አሸንፈን ወደ ቀጣይ ዙር ለማለፍ እና በመጀመርያው ተሳትፏችን ጥሩ ጉዞ ለማድረግ ነው እቅዳችን።

በአፍሪካ በውድድሮች ያለህ አንፃራዊ ልምድ ለቡድኑ ምን ጥቅም ይኖረዋል ብለህ ታስባለህ?

በግሌ ያለኝ ልምድ እንዳለ ሆኖ አዲስ ወደ ቡድኑ የተቀላቀሉት እና አንዳንድ ነባሮችም በውድድሩ ጥሩ ልምድ ነው ያላቸው። ሁላችንም በህብረት በመሆን ይህንን ዙር አልፈን በውድድሩ ላይ ጥሩ ጉዞ ለማድረግ ያግዘናል።

በዚህ ሰዓት ያለው የቡድናችሁ ስሜት ምን ይመስላል?

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ቻምፒዮን ነን፤ ውድድሩ ካለቀም ብዙ ግዜ አልሆነውም። አሁንም በቡድናችን ያለው ያንን የሻምፕዮንነት እና ጥሩ የማሸነፍ መንፈስ ነው። ይህንን ጨዋታ አሸንፎ ጥሩ ውጤት ይዞ መመለስ ነው እቅዳችን። ደስ የሚለው ነገር ደግሞ የመጀመርያ ጨዋታችን ከሜዳችን ውጭ መሆኑ ነው። በሁለተኛው ጨዋታ በሃገራችን በሜዳችን እና በደጋፍያችን ፊት ስለምንጫወት እንደምናልፍ እርግጠኛ ነኝ።

የቡድኑ አምበል እንደመሆንህ በዚህ ጨዋታ በውጤት ደረጃ ምንድነው እቅዳችሁ?

ኳስ ላይ ቀድመህ ውጤቱ እንዲህ ነው ማለት አትችልም። ተጋጣሚህን በደንብ ሳታይ እንዲህ ነው እንዲያ ነው ብለህ መናገር ከባድ ነው። ግን አሸንፈን ወይም አቻ ወጥተን ጥሩ ዕድል ይዘን ወደ ሁለተኛው ጨዋታ እንገባለን ብዬ በእርግጠኝነት እናገራለው። በሁለተኛው ጨዋታ ደግሞ የተሻለ የመዘጋጃ ጊዜም ስላለን የተሻለ ቡድን ይዘን ነው በሜዳችን የምንጫወተው።

ከጨዋታው በፊት ስለ ተጋጣሚያችሁ ምን መረጃ አግኝታችኋል?

አዎ አግኝተናል። ግብ ጠባቂያን ፍሊፕ ኦቮኖ ኢኳቶሪያል ጊኒያዊ ስለሆነ በሱ በኩል ጥሩ መረጃዎች አግኝተናል። መረጃዎቹም የተሻለ ዝግጅት እንድናደርግ ረድተውናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡