ሉሲዎቹ ለኦሊምፒክ ማጣርያ ጨዋታ ዝግጅታቸውን እያደረጉ ይገኛሉ

የኢትዮጵያ የሴቶች ኦሊምፒክ ብሔራዊ ቡድን በቶክዮ ኦሊምፒክ የማጣርያ ጨዋታ ከካሜሩን ጋር ነሐሴ 19 በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ለሚያደርገው ጨዋታ በአዳማ ዝግጅት በማከናወን ላይ ይገኛል።

ለ23 ተጫዋቾች ጥሪ ያደረገችው አሰልጣኝ ሠላም ዘርዓይ በአዳማ ኤክስኪዩቲቭ ሆቴል መቀመጫቸውን በማድረግ ዝግጅታቸውን ከጀመሩ ስድስተኛ ቀን አስቆጥረዋል። ጥሪ ከተደረገላቸው 23 ተጫዋቾች መካከል ግብ ጠባቂዋ ማርታ በቀለ በጉዳት ምክንያት ከብሔራዊ ቡድን ስብስብ ውጭ በመሆኗ በእርሷ ምትክ የቅዱስ ጊዮርጊሷ ከንባቴ ከተሌ ቡድኑ መቀላቀል ችላለች።

በዛሬው ዕለት ከ17 ዓመት በታች የወንዶች ቡድን ጋር የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ያደረጉ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪም ሐሙስ ወደ ኬንያ በማቅናት ቅዳሜ ከኬንያ ሴት ብሔራዊ ቡድን ጋር የአቋም መፈተሻ ጨዋታ የሚያደርጉ ይሆናል።

በዛሬው የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ላይ ግብ ጠባቂዋ ከንባቴ ከተሌ እና መዲና አወል በፓስፖርት ጉዳይ ተያይዞ ያልተገኙ ሲሆን ሴናፍ ዋቁማ በዛሬው ጨዋታ ላይ ጉዳት አስተናግዳ ወጥታለች። የተቀሩት የቡድኑ አባላት ግን በሙሉ ጤንነት ላይ ይገኘሉ።

ሉሲዎቹ የፊታችን ነሐሴ 19 በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም የሁለተኛ ዙር የመጀመርያ ጨዋታቸውን ከካሜሩን ያደርጋሉ።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡