ስሑል ሽረ ለቀጣይ ዓመት የሚጫወትበት ሜዳ ደረጃን የማሻሻል ሥራ ለመጀመር የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ እንደሚገኝ ተገለፀ።
በ2011 ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ያደገው ስሑል ሽረ የሜዳው ጨዋታዎቹን ሲያከናውንበት የነበረው ሽረ ስታዲየም የፕሪምየር ሊግ መመዘኛ የማያሟላ በመሆኑ በቀጣይ ዓመት ሜዳውን አድሶ ይቀርባል ወይስ ሌሎች ሜዳዎች ላይ ይጫወታል የሚለው አነጋጋሪ ነበር። በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ደንብ በፕሪምየር ሊጉ ጨዋታ እንዲደረግባቸው መመዘኛ የማያሟሉ ስታዲየሞች ለአንድ የውድድር ዓመት ብቻ አስተካክለው እንዲቀርቡ ጊዜ የሚሰጣቸው ሲሆን መመዘኛውን ካላሟሉ በተለዋጭ ሜዳ ጨዋታ ለማድረግ ይገደዳሉ። በዚህም ምክንያት ዘንድሮ ወልዋሎ የሜዳው ጨዋታዎቹ ወደ መቐለ እንደዞሩ የሚታወስ ነው።
ሜዳውን ሳር የማልበስ እና ተጓዳኝ ሥራ በመስራት በቀጣይ ዓመት ጨዋታዎቹን በሜዳው ለማከናወን ዝግጅት ማጠናቀቁን የክለቡ ፕሬዝዳንት አቶ ኪዳን ገብረመድን ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል። “ስሑል ሽረ በሜዳው ጨዋታዎችን ያደርጋል። ውድድሩ ከተጠናቀቀ ጊዜ አንስቶ ሜዳውን እንዴት መስራት አለብን የሚለውን እና ቅድመ ዝግጅት የሚያስፈልጋቸውን ነገሮች በመለየት ላይ ተንቀሳቅሰናል። ሜዳውን ሳር ለማልበስ አሁን ላይ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ደርሰናል። በዚህ ሥራ ላይ ብቁ የሆኑትን ለይተናል። በዚህ ሳምንት መጨረሻ ላይ አብረውን የሚሰሩትን ድርጅቶች በመለየት ነሐሴ 10 ላይ ወደ ሥራ እንገባለን። ጥቅምት መጨረሻ ላይም ሜዳው ለጨዋታ ይደርሳል። ከሜዳው ግንባታ በተጨማሪ የመልካች መቀመጫን ማሻሻል እንዲሁም የመፀዳጃ ቤቶች እና መልበሻ ክፍሎች ግንባታም በተጓዳኝ የሚሰሩ ይሆናል። ” ብለዋል።
የመጀመርያዎቹን ሦስት የሜዳው ጨዋታዎች በገለልተኛ ሜዳ እንዲጫወት የተቀጣው ክለቡ በዚህ ዙርያ ያለውን ሁኔታም ፕሬዝዳንቱ ገልፀዋል። “የመጀመሪያዎቹ ሦስት የሜዳችን ጨዋታዎችን ሜዳችን ላይ እንዳንጫወት ቅጣት አለብን። ይህንን ይግባኝ ብለናል፤ ነገር ግን ይግባኙ ውድቅ ከተደረግብን በትግራይ ኢንተርናሽናል ስታዲየም እንጫወታለን። ” ብለዋል።
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡