” አሸንፈን ለመመለስ በሙሉ አቅማችን እንፋለማለን” የአዛም አሰልጣኝ ኤቲዬን ንዳዪቭጊጄ

በታንዛንያ ዳሬ ሰላም መቀመጫቸውን ያደረገው አዛሞች በኮንፌደሬሽን ዋንጫ ከፋሲል ከነማ ጋር ላለበት የቅድመ ማጣርያ ዙር ጨዋታ ባህር ዳር ከተማ ከገቡ አራት ቀናትን ያስቆጠሩ ሲሆን ዛሬ ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ ጨዋታውን በሚያደርጉበት ስታዲየም የመጨረሻ ልምምዳቸውን አድርገዋል።

ከቡድኑ ባገኘነው መረጃ መሰረት በቡድኑ ምንም የጉዳት ችግር እንደሌለባቸው የገለፁልን ሲሆን ለአንድ ሰዓት በቆየው የዛሬው ልምምዳቸው በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ቀለል ያለ ልምምድ ከኳስ ጋር ሲያደርጉ ተስተውሏል። በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ላይ ደግሞ ለሁለት በመከፈል ጨዋታ ያደረጉ ሲሆን በፋሲል የኳስ ቁጥጥር አጨዋወት ላይ የተቃኘ የእርስ በእርስ ጨዋታ ሲያከናውኑ ታይተዋል። አጥቂዎችን ተጠቅመው ተጋጣሚን በራስ ሜዳ መገደብ፣ በተከላካይ ክፍል ብዙም እንቅስቃሴ ሳያደርጉ የመከላከል እና በመልሶ ማጥቃት የግብ እድል መፍጠር ላይ ያተኮረ የልምምድ ጨዋታ ተጫውተዋል።

ከልምምዱ በኋላ የአዛም አሰልጣኝ የሆኑት ኤቲዬን ንዳዪቭጊጄ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ተከታዩን አጭር ቆይታ አድርገዋል።

ባህር ዳር እና የአየር ፀባዩን እንዴት አገኛችሁት?

ባህር ዳር ቆንጆ ከተማ ነች። ቀዝቃዛ መሆኗ ተመችቶናል። ከመጣን አራት ቀን ሆኖናል፤ ከመጣን ጀምሮ ልምምዶችን ስንሰራ ነው የቆየነው። ጥሩ ጊዜ ነበሩ ያለፉት አራት ቀናት።

ስለ ተጋጣሚያችሁ ምን ያህል ታውቃላችሁ?

መረጃዎች አግኝተናል። ስለ ፋሲል ዩቲዩብ ላይ ቪዲዮ ተመልክቻለሁ። በተለይም የመጨረሻውን ጨዋታ (ሀዋሳን ያሸነፈበትን) አይቻለሁ። ጥሩ ቡድን እንደሆነ አይተናል።

አቅዳችሁ የመጣችሁት ምንድነው? ምን ያህልስ ዝግጁ ናችሁ?

አቅደን የመጣነው ለማሸነፍ ነው። ማሸነፍ ይቻላል፤ አየሩ ጥሩ በመሆኑ ለማሸነፍ ጥሩ አጋጣሚ ነው። በሥነ-ልቦና በጣም ዝግጁ ነን። ወደ ቀጣይ ዙር ለማለፍ ውጤቱን እንፈልገዋለን። አሸንፈን ለመመለስ እንደ ቡድን በጋራ እና በሙሉ አቅማችን እንፋለማለን ።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡