ቻምፒየንስ ሊግ| መቐለ 70 እንደርታ በካኖ ስፖርት በጠባብ ውጤት ተሸንፈዋል

በካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የመጀመርያ ጨዋታቸውን ለማድረግ ወደ ኢኳቶርያል ጊኒ ማላቦ ያመሩት የተጠናቀቀው የውድድር ዓመት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አሸናፊ መቐለ 70 እንደርታዎች በካኖ ስፖርት የ 2-1 ሽንፈት አስተናግደዋል።

ከአዲስ ፈራሚዎች መካከል ታፈሰ ሰርካን ብቻ በመጀመርያ አሰላለፍ በማካተት እና ኢኳቶርያል ጊኒያዊው ግብ ጠባቂ ፊሊፕ ኦቮኖን በአምበልነት በመጠቀም በተለመደው አሰላለፋቸው ወደ ሜዳ የገቡት ምዓም አናብስት በመጀመርያው የአፍሪካ ውድድራቸው እስከ 81ኛው ደቂቃ ድረስ 2-0 ሲመሩ የነበረ ሲሆን በተጠቀሰው ደቂቃ አማኑኤል ገብረሚካኤል ግብ በማስቆጠር ቡድኑን ከባዶ መሸነፍ ከማዳኑም ባለፈ ከሜዳው ውጭ ጥሩ ውጤት ይዞ እንዲወጣ አስችሏል።

ለመቐለ በታሪክ የመጀመርያ በሆነው የአፍሪካ መድረክ ጨዋታ በተከታታይ ዓመታት የቡድኑ ቁልፍ ተጫዋች የሆነው አማኑኤል ገብረሚካኤል ታሪካዊዋን የመጀመርያ ጎል ማስቆጠር ችሏል።

መቐለ 70 እንደርታዎች ባለፈው ሳምንት የትግራይ ስታዲየም የካፍ ፍቃድ ማግኘቱን ተከትሎ ከአስራ አምስት ቀናት በኋላ የመልስ ጨዋታቸውን በመቐለ ያደርጋሉ።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡