ቻን 2016 – ያልተዋሃደው ብሄራዊ ቡድናችን

አስተያየት – በሚካኤል ለገሰ

ቻን 2016 በሩዋንዳ አስተናጋጅነት ለ4ኛ ጊዜ ባሳለፍነው ቅዳሜ መጀመሩ ይታወሳል፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንም በምድብ ሁለት የመጀመሪያ ጨዋታውን ባሳለፍነው እሁድ ከዲ.ሪ. ኮንጎ ጋር አድርጎ 3-0 በሆነ ውጤት መሸነፉ ይታወሳል፡፡ ቡድኑ በኮንጎ በተሸነፈበት ጨዋታ የታየውንና ሊሻሻል የሚገባውን ደካማ ጎኖች ለመቃኘት እንሞክራለን፡፡

 

ወረቀት ላይ የቀረው 4-2-3-1 እና ያልተዋሃደው ቡድናችን

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከረጅም ጊዜያት በኃላ (በነጥብ ጨዋታ) በ4-2-3-1 የአጨዋወት ስልትን ተጠቅሟል፡፡ ከ4-2-3-1 ባህርይ አንፃር ቡድኑ በወረቀት ላይ በቅርብ ጊዜያት ካሳየው አቋም በተሻለ የተረጋጋ የሚመስል ፣ በማጥቃቱም ሆነ በመከላከል ረገድ ሚዛናዊ ቅርፅ እንደሚይዝ ቢጠበቅም በሜዳ ላይ ግን ሲተገበር አልተስተዋለም፡፡

በ4-2-3-1 ባለ 4 ረድፍ አሰላለፍ በመሆኑ በዘመናዊው እግር ኳስ በብዛት ሲተገበር የምናስተውለውን ፈጣን ሽግግር (ከመከላከል ወደ ማጥቃት እና ከማጥቃት ወደ መከላከል) ለመተግበር ተጫዋቾች በተሻለ አቋቋም ላይ እንዲገኙ የሚረዳ ቢሆንም ቡድኑ በመስመርም ይሁን መሃል ለመሃል የሚያደረገው የሽግግር እንቅስቃሴ ደካማ ነበር፡፡ በተለይ ይህንን ሚዛን የመጠበቅ ሀላፊነት መወጣት የነበረበት ጋቶች ይህንን ሲተገብር አልታየም፡፡ በ4-2-3-1 በሜዳው ቁመት ከተጋጣሚ ፍፁም ቅጣት ምት ጠርዝ እስከ ቡድናችን ፍፁም ቅጣት ምት ጠርዝ ያለውን ቦታ (Box to Box) በመሸፈን የቡድኑን የማጥቃት እና መከላከል ሚዛን መጠበቅ ፣ በዝግታ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመጠጋት (late run) ተጨማሪ የማጥቃት ኃይል መፍጠር እና በግብ ሙከራዎች የሚመለሱ ኳሶች (rebound) ላይ ቀድሞ የሚገኝበት አቋቋም ላይ መገኘት የሚጠይቀውን ታታሪነት እና የቦታ አያያዝ ክህሎት ከዋንኛው የተከላካይ አማካይ ተስፋዬ አለባቸው ጎን ከተሰለፈው ጋቶች ፓኖም መመልከት ነበረብን፡፡

ተስፋዬ አለባቸውም ዋንኛ ተግባሩ የነበረው የተከላካይ መስመሩን ሽፋን የመስጠት ተግባር በአግባቡ ሲወጣ አልታየም፡፡ ካፍ ካወጣው የጨዋታው ቁጥራዊ መረጃ መረዳት እንደሚቻለው ተስፋዬ አብዛኛውን ኳስ የነካው ከአጥቂ ጀርባ ባለው የሜዳ ክፍል ላይ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ከመሃል ተከላካዮቹ ኳስ በመቀበል ኳስ የማሰራጨት ተግባሩን ዘንግቶት ውሏል፡፡ በአንዳንድ አጋጣሚዎች ላይ ከአጥቂው ጀርባ ተሰልፎ የነበረው ኤልያስ ማሞ በጥልቀት ወደ ኋላ እየተመለሰ ኳሶችን ሲቀበል የተመለከትነውም ተስፋዬ ሚናውን በመዘንጋቱ ነው፡፡

ሌላው ከተከላካይ አማካዩ ማግኘት ያልቻልነው ጥቅም በጎንዮሽ እንቅስቃሴ የመስመር ተከላካዮች ትተውት የሚሄዱትን ክፍተት የመሸፈን ሚናን ነው፡፡ በኮንጎው ጨዋታ የተቆጠሩብን ሶስቱም ግቦች መነሻቸው ከመስመር መሆኑን ስናስተውል ይህን ሃሳብ ያጠናክርልናል፡፡

offensive balance

 

ደካማ የማጥቃት እንቅስቃሴ እና የቅብብል ስኬት  

ቡድኑ በእሁዱ ጨዋታ ላይ በአጠቃላይ 41% የኳስ ቁጥጥር ሲያስመዘገብ የተሳካ የኳስ ቅብብሎሽ ማድለግ የቻለው በመቶኛ 72% ነው፡፡ ቡድኑ ከወራት በፊት አስተናግዶት በነበረው የሴካፋ ውድድር ላይ በጨዋታ በአማካይ ከሚቀባበላቸው ኳስች 81% የተሳኩ ነበሩ፡፡ በዚኛው ጨዋታ ላይ ቀንሶ መታየቱ ተጋጣሚያቸን ምን ያህል አፍነው ሲጫወቱ እንደነበር የሚያሳይ ነው፡፡

ቡድኑ ወደፊት አለመሄድ ደግሞ ሌላኛው መሰረታዊ ችግር ነው፡፡ ቡድኑ ከተቀባበላቸው ኳሶች ግማሽ ያህሉ ወደፊት ሲሆኑ ቀሪዎቹ ወደ ኋላ እና ወደ ጎን የተቀባበሏቸው ናቸው፡፡ ከተከላካይ አማካዮቹ ፊት ዋንኛ የፈጠራ ምንጭ ሆኖ የተሰለፈው ኤልያስ ማሞ ካቀበላቸው 38 ኳሶች 30 ያህሉ የተሳኩ ቢሆንም ወደ ፊት ያቀበላቸው ኳሶች ብዛት 7 ብቻ ነው፡፡ የኤልያስ ደካማ እንቅስቃሴ የአማካይ ክፍሉ እና የአጥቂ ክፍሉ ተነጣጥሎ እንዲቀር አድርጎታል፡፡

ከቡድናችን ከፍተኛ የኳስ ቅብብሎችን ያደረገው የቀኝ ተከላካዩ ስዩም ተስፋዬ ነው፡፡ ስዩም 61 ያህል ኳሶችን ለመቀባበል ቢሞክርም አብዛኛዎቹ ቅብብሎች በራሳችን ሜዳ የተገደቡ እና በተጋጣሚ የሜዳ ክፍል ሲደርሱ የሚቆረጡ ነበሩ፡፡ ተቀይሮ ገብቶ ለ33 ደቂቃዎች ሜዳ ላይ ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው አስራት መገርሳ ቡድኑ ወደፊት ቶሎ ቶሎ እንዲሄድ የበኩሉን ሲያደርግ ተስተውሏል፡፡

ball direction

ቡድኑ በአጠቃላይ በጨዋታው 7 ሙከራዎችን ሲያደርግ ሁለቱ ብቻ ናቸው ኢላማቸውን የመቱት፡፡ ከሰባቱ አጋጣሚዎች ስድስቱ ከፍፁም ቅጣት ምት ውጭ የተሞከሩ ሲሆኑ ወደ ተጋጣሚያችን የፍፁም ቅጣት ምት ክልል በመግባት ሙከራ ማድረግ የቻልነው በአንድ አጋጣሚ ብቻ ነው፡፡ እነዚህ ቁጥሮች የሚያሳዩን የቡድኑን የፈጠራ ችግር ፣ ደካማ የቅብብል ስኬት እና የተደራጀ የማጥቃት ስትራቴጂ አለመኖር ነው፡፡

cross

የመስመር አጨዋወታችን ሌላው የቡድናችን ደካማ ጎን ነው፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በሙሉ 90 ደቂቃው ሁለቱም የመስመር ተከላካዮቻችን ያሻገሩት የኳስ ብዛት 2 ብቻ ነው፡፡ ቡድኑ መሃል ለመሃል ካደረገው የማጥቃት እንቅስቃሴ በባሰ መልኩ የመስመር አጨዋወታችን አጅግ ደካማ ነበር፡፡

የችግሮቹ ምክንያቶች ምንድን ናቸው?

ከላይ በርእሱ እንደተጠቀሰው ቡድኑ ያልተዋሃደ እና ለምን አይነት አላማ ወደ ሜዳ እንደሚገባ ግልጽ ያልሆነ ነው፡፡ በሜዳ ላይ የሚተገበሩ ፎርሜሽኖች እና ስትራቴጂዎች ከተጫዋቾች የአጨዋወት ባህርይ ጋር በሚስማማ መልኩ ካልተተገበረ ከስእላዊ መግለጫ ውጪ የሚፈይደው ነገር አይኖርም፡፡

ቡድኑ ለቻን ዝግጅት ከጀመረ ጀምሮ ሁሉም የልምምድ ፕሮግራሞች ለተመልካች ክፍት በመሆናቸው የሶከር ኢትዮጵያ ባልደረቦች ሁሉንም ልምምድ ተመልክተዋል፡፡ ነገር ግን አሰልጣኝ ዮሃንስ ቡድኑን ለሁለት ከፍለው ከማጫወታቸው እና የአካል ብቃት ልምምዶች ከመስጠታቸው ውጪ አንድም ጊዜ ይሄ ነው የሚባል ታክቲካዊ ልምምድ እና በጨዋታ ላይ ሊተገብሩ ያቀዱትን ስትራቴጂ ለተጫዋቾቻቸው በተግባር ሲያለማምዱ አልታየም፡፡ በዚህም ምክንያት እንደ ቡድን የተዋሃደ እና የተደራጀ እንቅስቃሴ ከቡድናችን ልንመለከት አልቻልንም፡፡

አሰልጣኝ ዮሃንስ ለተጫዋቾቻቸው የንድፈ ሃሳብ ትምህርት ሊሰጧቸው ቢችሉም ንድፈ ሃሳቡን በጨዋታ ላይ የሚተገብሩበትን ልምምድ (Drill) በየጨዋታ ሚናቸው ከፋፍለው የማጥቃት ፣ የመከላከል እና ኳስ የመቆጣጠር ስትራቴጂያቸውን በተጫዋቾች ላይ ሊያሰርፁ ይገባል፡፡

 

ለካሜሩን ጨዋታ ምን አይነት ለውጥ እንጠብቅ?

የኮንጎው ጨዋታ ላይ ተቀይሮ ሲገባ ቡድኑ ላይ የተሻለ አዎንታዊ ለውጥ ሲያሳይ የተስተዋለው አስራት መገርሳ በቋሚ 11 ውስጥ ሊካተት ይችላል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ አስራት በቡድኑ ላይ የሚታየውን መሰረታዊ የኳስ ስርጭት ችግርን ከተስፋዬ በተሻለ ሊቀርፍ ይችላል፡፡ ከሁለቱ የተከላካይ አማካዮች መካከል ለቡድኑ የማጥቃት እና የመከላከል እንቅስቃሴን በሚዛናዊነት ማበርከት ከተሳነው ጋቶች ፓኖም ይልቅ ታታሪነት እና ፍጥነት ያጣመረው ሳምሶን ጥላሁን በተሻለ ሚናውን ሊወጣ ይችላል፡፡

ሌላኛው አሰልጣኙ ለውጥ ያደርጋሉ ተብሎ የሚጠበቀው የግራ መስመሩ ላይ ነው፡፡ ታደለ መንገሻ በእሁዱ ጨዋታ ላይ ተቀይሮ ገብቶ በቀኝ መስመር ላይ ተሰልፎ ቢጫወትም አሰልጣኙ በግራ መስመር ላይ ያለባቸውን ክፍተት ለመድፈን ታደለን ያሰልፉታል የሚል ግምት አለ፡፡ የቀኝ እግር ተጫዋች የሆነው ታደለ በግራ መስመር ላይ ከተሰለፈ ለቡድኑ ተጨማሪ የፈጠራ ምንጭ ሊሆን ይችላል፡፡

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ሁለተኛ የምድብ ጨዋታውን ነገ 1፡00 ላይ ከካሜሩን ብሄራዊ ቡድን ጋር 10 ሺህ ተመልካች የመያዝ አቅም ባለው ስታዴ ሁዬ ጨዋታውን ያደርጋል፡፡ በዚህ ጨዋታ ላይ ምንም አይነት በጉዳም ሆነ በቅጣት ምክንያት ብሄራዊ ቡድናችን የሚያጣቸው ተጨዋቾች አለመኖራቸው ሌላ ለቡድኑ እንደ ጥሩ ነገር የሚጠቀስ ነው፡፡

 

መልካም እድል ለዋሊያዎቹ!!!

ያጋሩ