ሪፖርት| ፋሲል ከነማ አዛምን በሜዳው አሸነፈ

በካፍ ኮንፌደሬሽን ዋንጫ ቅድመ ማጣርያ የመጀመርያ ጨዋታ ፋሲል ከነማ የታንዛንያው አዛምን በባህር ዳር ዓለማቀፍ ስታዲየም አስተናግዶ 1-0 አሸንፏል።

በጨዋታው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ፣ የባህር ዳር ከተማ ከንቲባ አቶ ሙሉቀን አየሁ፣ የጎንደር ከተማ ከንቲባ አቶ ሙሉቀን አዳነ (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ ጨምሮ በርካታ ደጋፊዎች ተገኝተዋል። ጨዋታው ሁለት መልክ የነበረው ሲሆን በመጀመሪያው አጋማሽ ባለሜዳዎቹ ፋሲል ከነማዎች በሁለተኛው አጋማሽ ደግሞ ተጋባዦቹ አዛሞች ተሽለው የታዩበት ነበር።

በሚገርም የደጋፊ ድባብ ተሟሙቆ የጀመረው ጨዋታው በሙከራዎች የታጀበ ባይሆንም ጥሩ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ግን ታይቶበታል። ጨዋታው ገና እንደተጀመረ ጎል ለማስቆጠር ጫና የፈጠሩት ባለሜዳዎቹ በሦስት ደቂቃዎች ልዩነት ወደ አዛሞች የግብ ክልል ደርሰው ሙከራዎችን ሰንዝረዋል። በዚህም በ3ኛው ደቂቃ ኢዙ አዙካ በግራ መስመር ያገኘውን ኳስ እየገፋ ሄዶ ለሙጂብ ቃሲም በማቀበል የተሞከረ እንዲሁም በ6ኛው ደቂቃ የተገኘን የቅጣት ምት ሱራፌል ዳኛቸው አሻምቶት ሙጂብ በድጋሚ ያልተጠቀመበት አጋጣሚዎች ተጠቃሽ ናቸው። በጨዋታው ጅማሮ ሙሉ ለሙሉ የበላይነት የወሰዱት ፋሲል ከነማዎች ኳስ ይዘው ለመጫወት ሲሞክሩ ተጋባዦቹ አዛሞች ደግሞ ወደ ራሳቸው የግብ ክልል አፈግፍገው በጥብቅ የመከላከል አደረጃጀት ለመጫወት ሞክረዋል።

ምንም እንኳን ዐፄዎቹ በጨዋታው ኳስ ተቆጣጥረው መጫወት ቢችሉም የጠራ የግብ ማግባት አጋጣሚ ለመፍጠር ግን ተቸግረው ተይተዋል። የአዛምን የተከላካይ መስመር ተጨዋቾች ትኩረት ለመበታተን ቦታ በመቀያየር ሲጫወት የነበረው ኢዙ አዙካ በ15ኛው ደቂቃ ከርቀት አክርሮ በመታው ኳስ ፋሲሎች ወደ ግብ ቀርበው ነበር። ከሦስት ደቂቃ በኋላም ሱራፌል ዳኛቸው ከርቀት ለሙጂብ ያሻምውን ኳስ መቆጣጠር ያልቻሉት የአዛም ተከላካይ እና ግብ ጠባቂ መግባባት ተስኗቸው ራሳቸውን ለግብ አጋልጠው ነበር።

ከ20ኛው ደቂቃ በኋላ የተቀዛቀዘው ጨዋታው ሙከራዎችን ሳያስተናግድ ቀጥሏል። ቀስ በቀስ ወደፊት መውጣት የጀመሩት አዛሞች ረጃጅም ኳሶችን በመጠቀም ግብ ለማስቆጠር ሲጥሩ ተስተውሏል። በ35ኛው ደቂቃ የተላከን ረጅም ኳስ ለማዳን ጥረት ያደረገው ግብ ጠባቂው ሚኬል ሳማኬ ከብሩስ ካንግዋ ጋር ተጋጭቶ በመጎዳቱ በጀማል ጣሰው ተተክቷል። ከጉዳቱ በኋላ መረጋጋት የተሳናቸው ፋሲሎች በተወሰነ መልኩ በተጋጣሚያቸው ብልጫ ተወስዶባቸው ታይቷል። እስከ 41ኛው ደቂቃ ምንም የግብ ማግባት ሙከራ ያላደረጉት አዛሞች ፈጣኖቹን የመስመር ተጨዋቾቻቸው በመጠቀም የመጀመሪያ የግብ ማግባት ሙከራ አድርገዋል። በዚህ ደቂቃ አብደላ መሱድ ከኒኮላስ ዋዳዳ የተቀበለውን ኳስ አክርሮ መቶ የነበረ ቢሆንም ሳማኪን ተክቶ የገባው ጀማል ጣሰው አድኖበታል።

የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቆ በጭማሪ ሰዓት በግራ መስመር ወደ አዛሞች የግብ ክልል ያመሩት ፋሲሎች ግብ አስቆጥረው መሪ ሆነዋል። በዚህ ደቂቃ ከግራ መስመር የተሻገረውን ኳስ ሙጂብ በግምባሩ ጥሩ ቦታ ላይ ለነበረው በዛብህ መለዮ አቀብሎት በዛብህ ግብ አስቆጥሯል። በዚህም ውጤት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

በመጀመሪያው አጋማሽ ብልጫ የተወሰደባቸው ተጋባዦቹ በሁለተኛው አጋማሽ እጅጉን ተጠናክረው ቀርበዋል። ምንም እንኳን በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ ፋሲሎች ኳስን ለመቆጣጠር ቢጥሩም የአዛሞችን አጨዋወት መገደብ ግን ተስኗቸው ታይቷል። ጨዋታው በተጀመረ በ9ኛው ደቂቃ የመዓዘን ምት ያገኙት አዛሞች አጋጣሚውን ወደ ግብነት ለመቀየር ጥረው መክኖባቸዋል። በፈጣን ሽግግሮች እንዲሁም በረጃጅም ኳሶች አጨዋወታቸውን የቃኙት አዛሞች ከሁለት ደቂቃ በኋላም ወደ ፋሲል የግብ ክልል ደርሰው አስደንጋጭ ሙከራ ሰንዝረዋል። በመጀመሪያ አጋማሽ የያዙትን ብልጫ የተነጠቁት ፋሲሎች ሱራፌል በግል ጥረቱ እየገፋ ሄዶ በሞከረው ሙከራ ሁለተኛ ጎል ለማስቆጠር ሞክረዋል።

አዛሞች ከሚያደርጉት የመስመር ላይ ሽግግር በተጨማሪ የሚያገኟቸውን የቆሙ ኳሶች በመጠቀም ግብ ለማስቆጠር ጥረዋል። በዚህ የጨዋታ ሂደትም በ70ኛው ደቂቃ ብሩስ ካንግዋ በቀኝ መስመር ከሚገኘው የመዓዘን ምት መምቻ አካባቢ የተገኘውን የቅጣት ምት ተጠቅሞ ግብ ለማስቆጠር ሞክሮ ጀማል አውጥቶበታል። ከሦስት ደቂቃዎች በኋላም ዳግም እድል ያገኙት አዛሞች በኢድ ሰሌማን አማካኝነት ጥሩ እድል ፈጥረው ግብ ሳያስቆጥሩ ቀርተዋል። በተቃራኒው ፋሲል ከነማዎች ከ60ኛው ደቂቃ በኋላ ያገኙትን መሪነት ላለማጣት በሚመስል መልኩ ወደ መከላከሉ አመዝነዋል።

ምንም እንኳን የአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ቡድን ወደ መከላከሉ ቢያመዝንም ረጃጅም ኳሶችን ለኢዙ እና ለሙጂብ በመጣል አጋጣሚዎችን ለመፍጠር ሞክሯል። በ74ኛው ደቂቃ በዚህ የጨዋታ እንቅስቃሴ የተገኘን የመዓዘን ምትም ሱራፌል አሻምቶት ያሬድ በግምባሩ ሞክሮት ግብ ሊቆጠር ተቃርቦ ነበር። ፊት መስመራቸውን አጠናክረው ግብ ለማስቆጠር ያለሙት ተጋባዦቹም የተጨዋች ለውጦችን አድርገው ይብሱኑ ተጠናክረዋል። በ78ኛው እና በ79ኛው ደቂቃም ተቀይሮ ወደ ሜዳ በገባው ኢማኑኤል ምቩዬኩሬ አማካኝነት ጥሩ ጥሩ ሙከራዎችን ሰንዝረው ጀማል እና የግቡ አግዳሚ አምክነውባቸዋል። ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሁለት ደቂቃ ሲቀረው የቅጣት ምት ያገኙት ፋሲሎች አጋጣሚውን በሱራፌል አማካኝነት ወደ ግብ መተውት መሪነታቸውን ወደ ሁለት ከፍ ለማድረግ ጥረው ነበር። ጨዋታውም ተጨማሪ ግን ሳይቆጠርበት በፋሲል ከነማ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

የመልሱ ጨዋታ ዳሬ ሰላም ላይ ከ15 ቀናት በኋላ ይካሄዳል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡