የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ የማጠቃለያ ውድድር ዛሬ በአዳማ ከተማ ሲጀመር ወላይታ ድቻ እና መከላከያ በሰፊ ውጤት አሸንፈዋል።
6:00 ላይ የምድብ ሀ አሸናፊው ሀዋሳ ከተማን በምድብ ለ ሁለተኛ ደረጃ ይዞ ካጠናቀቀው አዳማ ከተማ ያገናኘው ጨዋታ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል። ሁለቱም ጎሎች በመጀመርያው አጋማሽ በተቆጠሩበት በዚህ ጨዋታ እንደተጠበቀው ጠንካራ ፉክክር ያልተደረገበትና በሙከራ ያልታጀበ ነበር። በ24ኛው ደቂቃ የሀዋሳው ምንተስኖት እንድሪያስ ከተከላካይ ጀርባ ጥሩ እድል አግኝቶ ወደ ግብ መጠጋት ሲችል በቀጥታ መትቶ ወደ ውጪ የወጣበት የመጀመርያው ሙከራ ሲሆን ከአንድ ደቂቃ በኋላ ወንድማገኝ እንደግ ከቀኝ መስመር ከርቀት አክርሮ መትቶ ግብ ጠባቂው ያወጣበት በአዳማ በኩል ጠንካራ ሙከራ ነበር። በ29ኛው ደቂቃ ሶሬሳ ዱቢሳ ከቅጣት ምት ያሻማውን ኳስ እዮብ ማቴዎስ በግንባሩ ገጭቶ በማስቆጠር አዳማ ከተማን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል።
ጨዋታው ከጎሉ መቆጠር በኋላ ተቀዛቅዞ በዚሁ ውጤት ወደ እረፍት ያመራሉ ተብሎ የዳኛ ፊሽካ ሲጠበቅ ብሩክ ዓለማየሁ ከቅጣት ምት የተሻማን ኳስ አስቆጥሮ ሀዋሳን አቻ አድርጓል።
ከእረፍት መልስ የነበረው የጨዋታ እንቅስቃሴ ከመጀመርያው ይበልጥ የተቀዛቀዘ ነበር። በዚህ አጋማሽ ሊጠቀስ የሚችለው ገና ጨዋታው አራት ደቂቃ እንዳስቆጠረ በአዳማ የግብ ክልል በተሰራ ጥፋት የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ተቀይሮ የገባው የሀዋሳው ሐብታሙ መኮንን ማምከኑ ነው።
በ55ኛው ደቂቃ የፍፁም ቅጣት ምቱን ያመከነው ሐብታሙ ከግራ መስመር አክርሮ መትቶ ግብ ጠባቂው ያወጣበት እና በአዳማ በኩል ከጥሩ አንድ ሁለት ቅብብል በኋላ ያብስራ አክሊሉ አክርሮ መትቶ ለጥቂት የወጣበትም የሚጠቀሱ ሙከራዎች ነበሩ። ጨዋታውም በመጀመርያ የው አጋማሽ በተቆጠሩ ጎሎች በአቻ ውጤት ተጠናቋል።
8:00 ላይ ወላይታ ድቻ ከአፍሮ ፅዮን ያደረጉት ጨዋታ በድቻ የበላይነት 5-1 ተጠናቋል። ከመጀመርያው ጨዋታ የተሻለ እንቅስቃሴ የታየበት ይህ ጨዋታ በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች ተመጣጣኝ ፉክክር ቢያስመለክተንም የኋላ ኋላ ወላይታ ድቻዎች የበላይነታቸውን አሳይተዋል። ጎል በማስቆጠር ቅድሚያ የወሰዱት አፍሮ ፅዮኖች በመሐመድ ኑረዲን የ3ኛ ደቂቃ ጎል ነበር። በግሉ ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው መሐመድ በ15ኛው ደቂቃም ከርቀት ሞክሮ የግቡ አግዳሚ መልሶበታል። በ17ኛው ደቂቃ አምበሉ ምስክር መለሰ ወላይታ ድቻን አቻ ያደረገች ጎል ያስቆጠረ ሲሆን ከጎሉ በኋላ ድቻዎች አይለው ታይተዋል። በተደጋጋሚ ከርቀት እና በተሻጋሪ ኳሶችም የጎል አጋጣሚ ለመፍጠር ጥረት ማድረግ ችለዋል። ሆኖም የመጀመርያው አጋማሽ ተጨማሪ ጎል ሳይቆጠርበት 1-1 ተገባዷል።
ሁለተኛው አጋማሽ ታምራት ሰላስ ደምቆ የወጣበት ነበር። በ53ኛው እና 58ኛው ደቂቃ አከታትሎ ያስቆጠራቸው ጎሎች ድቻን ወደ መሪነት ሲያሸጋግሩ በ65ኛው ደቂቃ ከተከላካዮች አምልጦ በመውጣት እና 90ኛው ደቂቃ ደግሞ ግብ ጠባቂውን በማለፍ ተጨማሪ ጎሎች (በአጠቃላይ በጨዋታው አራት ጎሎች) ማስቆጠር ችሏል። ጨዋታውም በወላይታ ድቻ 5-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።
10:00 ላይ በተከናወነው የዕለቱ የመጨረሻ ጨዋታ መከላከያ አፍሮ ፅዮንን 5-1 አሸንፏል። የአንድ ቡድን የበላይነት በታየበት በዚህ ጨዋታ መከላከያዎች በእንቅስቃሴም ሆነ በሙከራ ልቀው ውለዋል። 7ኛው ደቂቃ ላይ ዊልያም ሰለሞን የተከላካዮችን መዘናጋት ተጠቅሞ ቀዳሚውን የጦሩ ጎል ሲያስቆጥር ከደቂቃ በኋላ ፋሲሎች አፀፋ ለመመለስ በሚመስል እንቅስቃሴ ወደ ጎል ቀርበው የተሻገረውን ኳስ በረከት አበባው ሳይደርስበት ቀርቷል። በ20ኛው ደቂቃ ኤፍሬም ኃይሉ ከቅጣት ምት ከርቀት ሞክሮ ግብ ጠባቂው ያወጣበትም ፋሲልን አቻ ለማድረግ የቀረበ ነበር። ከዚህ ሙከራ በኋላ ሙሉ ለሙሉ ብልጫ የወሰዱት መከላከያዎች በተደጋጋሚ ወደ ግብ የደረሱ ሲሆን በ29ኛው ደቂቃ ሰለሞን ሙላው ሁለተኛውን አክሏል። በ39ኛው ደቂቃ ደግሞ ዊልያም ሰለሞን ለግሉ ሁለተኛ ለቡድኑ ሦስተኛ ጎል አስቆጥሮ የመጀመርያው አጋማሽ በመከላከያ 3-0 መሪነት ተጠናቋል።
ከእረፍት መልስ የነበረው የጨዋታ እንቅስቃሴ ከመጀመርያው ጋር ተመሳሳይ መልክ የነበረው ሲሆን በቀላሉ ወደ ፋሲል የጎል ክልል ሲደርሱ የነበሩት መከላከያዎች በ51ኛው ደቂቃ አቤል ነጋሽ እና በ62ኛው ደቂቃ ሰለሞን ሙላው ተጨማሪ ጎሎች 5-0 መምራት ችለዋል። ከጎሎቹ በኋላ ጨዋታው የተቀዛቀዘ ሲሆን ተቀይሮ የገባው ዣቪየር ሙሉ በ83ኛው ደቂቃ ከርቀት የተገኘውን ቅጣት ምት በቀጥታ መትቶ ባስቆጠራት የማስተዛዘኛ ጎል ጨዋታው በመከላከያ 5-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ቀጣይ መርሐ ግብር
ማክሰኞ ነሐሴ 7 ቀን 2011
04:00 | አዳማ ከተማ ከ ወላይታ ድቻ
06:00 | ሀዋሳ ከተማ ከ መከላከያ
08:00 | አፍሮ ፅዮን ከ ፋሲል ከነማ
*ሁሉም ጨዋታዎች በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ይደረጋሉ
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡