የግል አስተያየት| የተጫዋቾች የደሞዝ ጣሪያ ጉዳይ…

በሚካኤል ለገሰ

ከሁለት ቀናት በፊት ቢሾፍቱ ላይ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የስፖርት ኮሚሽን ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጋር በተባበር የተጫዋቾች የደሞዝ ጉዳይ ላይ ውይይት በማድረግ ከፍተኛው የክፍያ መጠንን መገደቡ ይታወሳል።በዚህ መሰረት የተጫዋቾች የደሞዝ ጣሪያ 50ሺ ብር እንዲሆን ተወስኗል። 

ከዚህ ቀደም የጉዳዩ አሳሳቢነት ማለትም የተጫዋቾች ክፍያ በየጊዜው እያሻቀበ መምጣት በግልፅ የሚታይ እንደመሆኑ ውሳኔው መነጋገርያ መሆኑ አልቀረም። ፌዴሬሽኑ ከእግርኳሱ የእድገት ደረጃ ጋር በማይመጣጠን መልኩ ፈር ለቆ የነበረው የደሞዝ አከፋፈልን ለመግታት የሰጠው ትኩረት መልካም ቢሆንም ለዘላቂው መፍትሄ ከውሳኔው ጋር የተያያዙ ክፍተቶችን መመልከትም አስፈላጊ ነው።

በኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ለውጦች የሚከሰቱት ድንገት ነው። ለተጫዋቾች የሚከፈለው ክፍያም ከሀገሪቱ አጠቃላይ የኢኮኖሚ ደረጃ እና የግሽበት መጠን ጋር በማይነፃፀር መልኩ በፍጥነት ያሻቀበበትን ምክንያት ማወቅ አዳጋች ነው። ሆኖም ግልፅ ያልሆነው የፋይናንስ አካሄዳችን ለብልሹ አሰራር የተጋለጠ በመሆኑና በርካታ አካላትን አላግባብ ተጠቃሚ ለማድረግ በር የከፈተ በመሆኑ ያለ ከልካይ ዋጋ በማናር ከግሽበቱ ተጠቃሚዎችን ማፍራቱ የአደባባይ ሚስጥር ነው። ክለቦች ለተጫዋቾች የሚያወጡት ገንዘብ ከምክንያታዊነቱ ይልቅ ወቅታዊውን የገበያ ዋጋ ላይ የተመረኮዘ በመሆኑም በየትኛውም ደረጃ ላይ የሚገኝ ተጫዋች ያሻውን ደሞዝ እንዲጠይቅ በር መክፈቱም ለብዙዎች የተሰወረ ጉዳይ አይደለም። አሁን አሁን እየታየ ያለው ገደብ አልባ የሆነው የክልል ክለቦች በጀትም ለደሞዝ መናር ትልቁን ሚና እየተወጣ ይገኛል። ከእግርኳሳዊነት የዘለለው የክልሎች ፉክክርን በበላይነት ለመወጣት የሚደረገው ትንቅንቅ ክለቦችን ልቅ ለሆነ አላስፈላጊ ወጪ ሲዳርግ እየተመለከትን እንገኛለን። አፍጥጠው ከወጡ ምክንያቶች ባሻገር በርካታ ውስብስብ ምክንያቶች ሊኖሩት የሚችሉት ይህ የተጫዋቾች ደሞዝ መናር በወጉ ጥናት ቢደረግበት ከዓመት ወደ ዓመት ያሻቀበበትን ትክክለኛ ምንጭ ለመለየት ያስችላል። 

ወደ ዓርቡ ስብሰባ ስንመለስ የተጫዋቾች ደሞዝ ጣርያን ለመወሰን በቂ ጥናቶች ተደርገዋል ተብሎ አይታመንም። እንዲሁ በግርድፉ ከሌሎች የአፍሪካ ሃገራት የበለጠ ክፍያ ልንከፍል አይገባም፣ በጀታችንን እና የሀገር ኢኮኖሚን እየተፈታተነ ነው እና ተመሳሳይ ምክንያቶችን በማንሳት በፍጥነት ወደ ውሳኔ የተገባበት መንገድ ዘለቄታዊ መፍትሄ ለመስጠት ከመንደርደር ይልቅ የዱብ እዳ ያህል የፈጠነ ነበር ማለት ይቻላል። በዋነኝነት መጤን የነበሩባቸው ጉዳዮችም በድንገቴው ውሳኔ ሳይታዩ ቀርተዋል። 

በመጀመሪያ ውይይቱ የተደረገበት እና ውሳኔ የተላለፈበት ጊዜ ሊያነጋግር የሚችል ነው። የዝውውር መስኮት ከተከፈተና የእግርኳሱ አካላት በተለመደው አካሄድ ተጫዋቾችን ማስፈረም ከጀመሩ በኋላ ድንገት ውሳኔውን ማስተላለፍ መደነጋገርን መፍጠሩ አይቀርም። በአንድ ቀን ጥናት ቀርቦ፣ ውይይት ተደርጎ እና ሃሳብ ተንሸራሽሮ የሚወሰንን ውሳኔ ተፈፃሚነት ለማሰብ ከባድ ነው። ውይይት የተደረገበትን መንገድ እንኳን ስንመለከት ዋናዎቹን ተዋንያን (ተጨዋቾችን) ሳያማክል መሆኑ ያስገርማል። ነገሩ የቀጣሪ እና የተቀጣሪ ጉዳይ ሆኖ ሳለ ቀጣሪዎች ብቻ ተሰብስበው መወሰናቸው አጠያያቂ ነገሮችን ያስነሳል። ከምንም በላይ ግን ውሳኔው የችኮላ መሆኑን የሚያሳየው የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑን የመረጠው እና የሃገሪቱን እግር ኳስ የሚመሩ ግለሰቦች ጨምሮ በርካታ የእግር ኳስ አካላትን የያዘው ጠቅላላ ጉባዔ ሳይወያይበት መፅደቁ ነው። በዕለቱ ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ ጂራ በሊግ ፎርማት ጉዳይ ላይ ለተነሳው ጥያቄ ውሳኔው በጠቅላላ ጉባዔ እጅ ላይ መሆኑን ቢገልፁም የደሞዝ መገደብ ጉዳይ በዕለቱ የተገኙ ተሰብሳቢዎች ጉዳይ ብቻ መሆኑ አነጋጋሪ ነው።

ውሳኔው የሚፈፀምበት አካሄድ ባልተገለፀበት፣ በውስጡ የያዛቸው ደንቦች ባልተብራሩበትና ግንዛቤ ባልተፈጠረበት ሁኔታ ድንገት ውሳኔ ላይ መድረስ ነገሮችን ወደሌላ ውስብስብ ችግሮች እንድናመራ በር የሚከፍት ነው። ይልቁንም ጊዜ ተወስዶበት ሰፊ ጥናት እና ውይይት ተደርጎበት፣ ሁሉንም አካላት አሳታፊ ባደረገ መልኩ ውሳኔ ቢተላለፍ ዘለቄታዊ መፍትሄ ማበጀች ይቻል ነበር። 

ሌላው የጊዜ ገደብ ነው። የትኛውም ዓይነት ውሳኔ የጊዜ ገደብ ያስፈልገዋል። ይህ የእግርኳሱን ከባቢ በአንድ ጊዜ ሊቀይር የሚችል ውሳኔ በድንገት “ከዛሬ ጀምሮ ተፈፃሚ ይሆናል” በሚል ማስተላለፍ የሚፈጥረው መደነጋገር ቀላል አይሆንም። ውሳኔው ተጠቃሚ የሚያደርጋቸው ክለቦች በለውጡ ይበልጥ እንዲጠቀሙ፤ ተጎጂ ሊሆኑ የሚችሉትም በሒደት ከውሳኔው ጋር እንዲላመዱ የተፈፃሚነት ፍኖተ ካርታ አዘጋጅቶ የጊዜ ገደብ ቢበጅለት ተመራጭ ይሆን ነበር። በአንድ ጊዜ ውሳኔውን ሙሉ ለሙሉ ለማስፈፀም ከመሞከር ይልቅ ደረጃ በደረጃ ወደ ግቡ መድረስ የውሳኔው አካል ሊሆን ይገባ ነበር። 

ውሳኔውን ከሀገሪቱ የፋይናንስ ሥርዓት ግልፅነት ጋር እንዴት አብሮ ማስኬድ ይቻላል የሚለውም ሊተኮርበት የሚገባ ጉዳይ መሆን ነበረበት። የክለቦች አጠቃላይ ሐብት፣ ዓመታዊ በጀት፣ ገቢ እና ወጪ እንዲሁም የገንዘብ ምንጭ በግልፅ በማይታወቅበት ሁኔታ፤ ዓመታዊ የኦዲት ምርመራ በማይደረግበት አኳኋን ይህን ውሳኔ ተግባራዊ ማድረግ ፈታኝ መሆኑ አይቀርም። 

ከመጋረጃ ጀርባ የሚከወኑ ተለምዷዊ አካሄዶችን በምን መልኩ ተቆጣጥሮ ውሳኔውን ተግባራዊ ያደርጋል የሚለውም መታየት ነበረበት። በእግርኳሳችን ፋይናንስን የሚመለከቱ ውስብስብ ጉዳዮች ቀርቶ በፊፋ እና ካፍ የተቀመጡ ግልፅ የእግርኳስ ህግጋትን ማስከበር ፈታኝ እንደሆነ ስንመለከት ቆይተናል። ከደሞዝ ጋር ተያይዘው የሚመጡ ደንቦች ደግሞ በርካታ የመቆጣጠርያ መንገዶች ሊበጁለት የሚገባ ነው። በስውር የሚደረጉ ስምምነቶች፣ በህግ ክፍተት ተጠቅመው በጥቅማጥቅም እና ቦነስ ሰበብ የሚወጡ ወጪዎችን መቆጣጠር እና የመሳሰሉት ከውሳኔው ጋር አብሮ ሊታይ ይገባል።

ሀገሪቱ የምትከተለው ነፃ ገበያ ኢኮኖሚ፣ የአሠሪና ሠራተኛ ህግ እና ሌሎች ተያያዥ ህግና ፖሊሲዎች ከግምት የገቡበት ውሳኔ ስለመሆኑም የሚያጠራጥር ነው። መቼም እነዚህ የሀገሪቱ ደንቦች በድንገት በተጠራ ስብሰባ ለምክክር ቀርበው ከሀገሪቱ ህጎች ጋር መጣረሰ አለመጣረሳቸው ከግምት ውስጥ ይገባል ብሎ መጠበቅ አስቸጋሪ ነው።

ከላይ የተጠቀሱት ጉዳዮች ከግምት ውስጥ ገብተው ውሳኔው እንደተወሰነ ብናስብ እንኳ ክለቦች ይህንን ደንብ ተፈፃሚ የሚያደርጉበት አስገዳጅነት እስከምን ድረስ ነው? ባያደርጉ ሊደርስባቸው የሚችለው የህግ እርምጃ ምንድነው? የሚሉ እና የመሳሰሉት ጥያቄዎች ተብራርተው ሳይቀመጡ ተግባራዊ እንዲሆን መወሰን የኋላ ኋላ ውዝግብ መፍጠሩ አይቀሬ ይሆናል።

የውሳኔው ተስፋ እና ሥጋት

የሆነው ሆኖ ውሳኔው “በአብላጫ ድምፅ” ተወስኗል። ከዓርብ ጀምሮም ውሳኔው ተፈፃሚ እንደሚሆንና ኮንትራት ያላቸው ተጫዋቾች ውላቸው ፈርሶ በአዲሱ ጣርያ መሠረት ደሞዛቸው እንዲከፈላቸው ተወስኗል። ከላይ ከውሳኔው በፊት ሊታዩ የሚገባቸው ጉዳዮች እንዳሉ ሆነው በዚህ ደንብ ተስፋ እና ሥጋት ዙርያ ጥቂት ነጥቦች እናንሳ። 

ተስፋዎች

– ውሳኔው ዞሮ ዞሮ በትክክል ተተገበረም አልተተገበረም አላግባብ የሚወጣውን የክለቦች ወጪ መቀነሱ አይቀሬ ነው። ገዳቢ ህጎች ካልወጡ በቀር በእቅድ መመራትና ወጪን መቀነስ ዳገት የሆነባቸው ክለቦቻችን በውሳኔው ቢያንስ የደሞዝ ወጪን ማቅለላቸው ትሩፋቱ ለእግርኳሱ ብቻ ሳይሆን በእግርኳስ ስም በሚወጣ ወጪ ምክንያት የልማት ሥራ ላልጎበኘው መከረኛ ህዝብ ነው። 

– ይህ ውሳኔ ተጫዋቾች ደረጃቸው ከፍ ወዳሉ ሊጎች እንዲያመሩ በር ሊከፍት ይችላል። በሀገራችን የሚታየው የደሞዝ አከፋፈል ተጫዋቾቻችንን ለስንፍና ያጋለጠ መሆኑ በግልፅ እየታየ ነው። ራስን ከፍ ወዳለ ደረጃ ለማድረስ እና ለመሻሻል ዳተኝነት የፈጠረ በመሆኑ ምናልባትም የደሞዝ ገደቡ ተጫዋቾቻችን ለተሻለ የኢኮኖሚ ጥቅም እንዲተጉ እና ደረጃቸው ከፍ ወዳሉ ሊጎች ለማምራት እንዲያልሙ በር ይከፍት ይሆናል። 

-ወጣት ተጫዋቾች እንዲበራከቱ ሊያደርግ ይችላል። በተለይም ለኑሮ ተመራጭ ያልሆኑ ከተሞች በደሞዝ ገደቡ ምክንያት ተጫዋቾችን ተደራድረው ማምጣት የሚቸግራቸው በመሆኑ ፊታቸውን ወደ አካባቢያቸው ወጣቶች ብሎም ወደ ወጣት ቡድኖች እንዲያዞሩ ሊያደርጋቸው ይችላል።

-የደሞዝ መጠኑ መገደብ አሳማኝ ባልሆነ ምክንያት ከውጪ ሀገራት ወደ ኢትዮጵያ እየፈለሱ የሚገኙት የውጪ ዜጋ ተጫዋቾችን ሊገታ ይችላል። ይህም ለሀራችን ተጫዋቾች የመጫወት እድልን ይሰጣል። ምንም እንኳን ለበርካታ የአፍሪካ ሀገራት ተጫዋቾች ከገደቡ በኋላ የሚከፈለው ክፍያ አሁንም ሳቢ ቢሆንም በቀደመው ከፍተኛ ክፍያ የመጡት ተጫዋቾች የብቃት ደረጃ አሳማኝ አለመሆንን ስንመለከት በአዲሱ የክፍያ መጠን የሚመጡ ተጫዋቾች ከቀደሙት የተሻሉ ይሆናሉ ብሎ መጠበቅ የዋህነት ይሆናል።

– የተረጋጉ ቡድኖችን ሊፈጥር ይችላል። የደሞዝ ከዓመት ወደ ዓመት መናር ተጫዋቾችን እንዳይረጋጉ ሲያደርግ ይታያል። ከዚህ ቀደም የተለመደው በየዓመቱ ክለብ የመቀያየር ባህል አሁን አሁን በየመንፈቁ ሆኗል። በየክለቡ ተቀራራቢ ደሞዝ የሚከፈል ከሆነ ግን ተጫዋቾች ክለብ ከመቀያየር ይልቅ በአንድ ክለብ በመርጋት ራሳቸውን የሚያሻሽሉበት፤ ክለቦችም ወጥ የሆነ ማንነት ያለው ቡድን የመገንባት እድል ሊሰጣቸው ይችላል።

የውሳኔው ሥጋቶች

– ምን አልባት ውሳኔው ከዝውውር መስኮቱ መከፈት ቀደም ብሎ ቢደረግ እና ተጨዋቾች አምነውበት አዳዲስ ውሎች ቢፈፅሙ የተሻለ ነበር። ሆኖም ውሳኔው ድንገት በመወሰኑ ተጫዋቾችን ያልታሰበ ቀውስ ውስጥ ሊያስገባ ይችላል። ለምሳሌ በዝውውር መስኮቱ በይፋ ተደራድረው የፈረሙ ተጨዋቾች የሚያገኙትን ገንዘብ አስልተው ከእግርኳሱ ጎን ለጎን የግል ሥራዎች ላይ ማዋል ከጀመሩ፤ ለዚህ አላማቸው ማስፈፀምያ ደሞዛቸውን ተማምነው ብድር ውስጥ ለገቡ ተጫዋቾች ውሳኔው ዱብ እዳ ይዞባቸው እንደሚመጣ እሙን ነው። 

– ውሳኔው የተጨዋቾችን ከቦታ ቦታ እንቅስቃሴ ሊገድበ ይችላል። ሁሉም ክለቦች የሚከፍሉት ክፍያ በጣም ተቀራራቢ ከሆነ እና በየክለቡ ያን ያህል የክፍያ ልዩነት ከሌለ ተጨዋቾች በቋሚ መኖሪያ አካባቢያቸው ብቻ እንዲጫወቱ ያደርጋል። ይህም ከወቅታዊው የአካባቢያዊነት ችግር ጋር ተዳምሮ ሌሎች ቀውሶችን ይዞ ሊመጣ ይችላል።

– ቀድሞውንም አናሳ የነበረው የተጨዋቾች ተነሳሽነት ይበልጡኑ ዝቅ ሊያደርገው ይችላል። በአንድ ቡድን ውስጥ በቋሚነት የሚሰለፍ ተጫዋች እና በተቀያሪነት የሚሰለፍ ተጨዋች የሚያገኙት የገንዘብ መጠን ተቀራራቢ ከሆነ ለተሰላፊነትም ሆነ ራስን ለማሻሻል የሚደረግን ጥረት ይገታል። 

– በአግባቡ ቁጥጥር ካልተደረገበት መንግስት ከግብር ማግኘት ያለበትን ገንዘብ ሊያሳጣ ይችላል። እንኳን እንዲህ ጣሪያ ተበጅቶለት በቀደሙት ጊዜያት ከፍተኛ ደሞዝ እየተከፈለም ለመንግስት መግባት የሚኖርበት ግብር በተገቢው መንገድ ሳይሰበሰብ ቆይቷል። አሁን ደግሞ የደሞዝ ጣርያው ለመንግስት የሚገባውን የግብር መጠን ይበልጥ ከማሳነሱ ባሻገር ክለቦች ተጨዋቾችን ለማማለል ከመጋረጃ ጀርባ የሚፈፅሙት ክፍያ ከመንግስት እውቅና ውጪ እንዲሆን ያደርገዋል።

ከደሞዝ ገደብ በተጓዳኝ ሊታዩ የሚገባቸው ሌሎች አማራጮች

ከላይ በፅሁፉ ለማሳየት እንደተሞከረው ክለቦች አላግባብ የሚያወጡት ወጪ ገደብ ሊበጅለት እንደሚገባ ሁሉ ለእግርኳሱ እድገት በሚበጅ መልኩ እንዲሆን ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ በርካታ የመፍትሄ ሀሳቦች ቀርበው የእያንዳንዱ አዋጪነት በሚገባ ታይቶ ወደ ውሳኔ ልንሄድ ይገባል። ክለቦችን እየተፈታተነ የሚገኘውን ወጪ ልጓም ለማበጀትም ከደሞዝ ገደብ በተጨማሪ ሌሎች የመፍትሄ ሀሳቦች በተጓዳኝ ሊታዩ ይገባሉ። 

*የአጠቃላይ ደሞዝ ወጪ ገደብ 

ከላይ የደሞዝ ጣርያው ሲወሰን ከግምት ውስጥ ሊገቡ የሚገባቸው ጉዳዮች በተለይም የፋይናንስ ግልፅነት እንዳለ ሆኖ ከቁርጥ የደሞዝ ጣርያ ይልቅ አጠቃላይ የደሞዝ ወጪን መገደብ የተሻለው አማራጭ መሆን ይችላል። በቡድኑ ውስጥ የሚገኙ ተጫዋቾች የብቃት ደረጃ ተመሳሳይ ባለመሆኑ የሚከፈላቸው ደሞዝም በተመሳሳይ ሊለያይ ይችላል። አንዱ ክለብ ከሌላኛው በተሻለ ደሞዝ ከፍሎ ተጫዋቾችን የግሉ ለማድረግ አዲሱ ገደብ እክል ሊሆንበት ይችላል። ስለዚህም አንድ ክለብ ለደሞዝ የሚያወጣው አጠቃላይ ወጪ በገደብ ቢቀመጥለት በተሻለ ነፃነት እንዲንቀሳቀስ ያደርገዋል። ለምሳሌ አንድ ክለብ ሊያወጣው የሚገባው አጠቃላይ ከፍተኛ ወርሀዊ የደሞዝ መጠን 2 ሚልዮን ቢሆን በክለቡ ከፍተኛ ደረጃ ለሚሰጣቸው ተጫዋቾች ካስፈለገም ከ50 ሺህ ብር በላይ በመክፈል ከሌሎች ዝቅተኛ ተከፋዮች ጋር በማሰባጠር የተመጣጠነ ቡድን የመገንባት እድልን ይፈጥርላቸዋል። 

*ክለቦችን “ክለብ” እንዲሆኑ ማስገደድ

አሁን አሁን በተለይ የክልል ክለቦች ከግብር ከፋዩ ህብረተሰብ የሚሰበሰበውን ገንዘብ ያለአግባቡ ወደ እግር ኳሱ እያመጡ ብክነቶችን ሲፈፅሙ በግልፅ ይታያል። በደሞዝ ሰበብ የሚወጡ ወጪዎችን ለመግጋት ከደሞዝ ጣርያ ይልቅ ክለቦች ለውድድር ሲቀርቡ ሊያሟሉ የሚገባቸው መመዘኛዎችን በማስቀመጥ ትኩረታቸውን በሙሉ መመዘኛ ወደማሟላት እንዲያተኩሩ ማድረግ ይቻላል። አንድን ክለብ ከመሰረታዊ የፅህፈት ቤት ከቋሚ ሰራተኞች ጋር፣ ብቁ ስታዲየም፣ የተሟሉ የዕድሜ እርከን ቡድኖች፣ አካዳሚ፣ ደረጃውን የጠበቀ የልምምድ ሜዳ፣ የተሟላ የባለሙያዎች ስብስብ፣ የሚዲያ፣ የቴክኒክ፣ የህክምና፣ የአገልግሎት እና የመሳሰሉት ዲፓርትመንቶች ጀምሮ ትንንሽ እስከሚመስሉን ነገር ግን ለእግርኳሱ አስፈላጊ እስከሆኑ ጥቃቅን ጉዳዮች ድረስ አሟልተው እንዲቀርቡ ማስገደድ ይገባል። ክለቦች ለእነዚህ ግዴታዎች የሚያስወጡት ወጪ ከፍተኛ በሆነ ቁጥር ለደሞዝ የሚያወጡት የገንዘብ መጠንም በራሱ ጊዜ ይገደባል። ለሚያወጡት እያንዳንዱ ወጪም ምክንያታዊ መሆንም ይጀምራሉ።

ከዚህ ጋር ተያይዞ በአውሮፓ እየተተገበረ የሚገኘው የፋይናንስ ስፖርታዊ ጨዋነት ደንብም አብሮ ሊታይ የሚገባው ነው። ዓመታዊ የኪሳራ መጠናቸውን በመገደብ ወጫቸውን እንዲቀንሱ የሚያደርጉ ደንቦችን ወደ እግርኳሳችን ማምጣት እንችላለን።

*መንግስት

የእግርኳሳችን ከመጠን ያለፈ የገንዘብ አወጣጥን ለመገደብ ከሁሉም በላይ ከመንግስት የቀረበ አካል አይገኝም። 3/4ኛ የሚሆኑ ክለቦች ከመንግስት ቀጥተኛ በጀች እየተመደበላቸው ያለአንዳች ትርፍ ይልቁንም ማኅበራዊ ቀውስ ወደማምጣት መሸጋገራቸው መንግስትን ሊያሳስብ ይገባል። ክለቦች ራሳቸውን እንዲችሉ፣ ከመንግስት/ከተማ አስተዳደር ተጠሪነት ተላቀው በሁለት እግራቸው እንዲቆሙ ማድረግ የመንግስት ግዴታ መሆን አለበት። የተጠቀሱት ጉዳዮች በተይም ራስን መቻል በአንድ ጀንበር ሳይሆን በሒደት የሚከወን በመሆኑ ለጊዜው የሚበጀትላቸውን ዓመታዊ በጀት በመቀነስ/በመገደብ ልቅ የገንዘብ አወጣጣችንን ፈር ማስያዝ ይቻላል። በእርግጥም ክለቦች በጀታቸው የተገደበ እና በጊዜ ሒደት በራሳቸው አቅም የሚያመነጩት እንዲሆን ከተደረገ ምክንያታዊ ያልሆነና ከልክ ያለፈ ደሞዝ ይከፍላሉ ተብሎ አይታሰብም።