ፋሲል ከነማ አዲስ አሰልጣኝ ቀጥሯል

ፋሲል ከነማ ከአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ጋር ከተለያየ በኋላ ለአሰልጣኝ ቅጥር ማስታወቂያ በማውጣት አሰልጣኝ ሥዩም ከበደን ለመቅጠር ከውሳኔ መድረሱን ትናንት መዘገባችን ይታወሳል። አሁን ባገኘነው ዜና መሠረትም አሰልጣኙ ቡድኑን ለማሰልጠን መስማማታቸውን ለማወቅ ተችሏል።

ፋሲል ከነማ አዛምን በጠባብ ውጤት በሜዳው አዛምን ካሸነፈ በኋላ ለሁለት ቀናት እረፍት ላይ የሚገኝ ሲሆን ከነገ በኋላ ወደ ልምምድ ይመለሳል። አሰልጣኝ ሥዩም ከበደም ቡድኑን እየመሩ የመጀመሪያ ልምምዳቸውን ያሰራሉ ።

አዲሱ የዐፄዎቹ አሰልጣኝ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረጉት አጭር ቆይታ የቡድኑን ጥንካሬ ማስቀጠል ላይ ትኩረት እንደሚያደርጉ ገልፀዋል። “ክለቡ ጥሩ የውድድር ዓመት ነበር ያሳለፈው። ስለዚህም የነበረውን ጥሩ ነገር በማስቀጠል የተሻለ ነገር ለመስራት ነው እቅዴ። ቡድኑን የበለጠ በማጠናከር ያሉትን ችግሮች በመቅረፍ የተሻለ ነገር ለመስራት እና ክለቡን ባለበት ትልቅ ደረጃ ማስቀጠልን አቅጃለሁ። ” ብለዋል።

በኮንፌዴሬሽን ዋንጫው ጨዋታ ላይ ቡድኑን በስታዲየም ተገኝተው የተመለከተለት አሰልጣኙ በጨዋታው የነበረውን ክፍተት በመልሱ ጨዋታ ለማስተካከል እንደሚሰሩ ጠቁመዋል። “የትናንቱ ጨዋታ ጥሩ የነበረ ቢሆንም የተወሰኑ ክፍተቶች አሉ። ለመልሱ ጨዋታ እነሱን እናስተካክላለን። ቡድኑን ከኔ ይበልጥ ረዳቶቸ ያውቁታል። ከነርሱ ጋር በመተጋገዝ ጨዋታውን አሸንፈን ወደ ቀጣይ ዙር ለማለፍ ነው እቅዳችን። ከነገ በኋላ ለጨዋታው ጠንካራ ዝግጅት እንጀምራለን።” ሲሉ አጠቃለዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡