የኢትዮጵያ ከ15 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድንን አስመልክቶ መግለጫ ተሰጠ

በኤርትራ አዘጋጅነት በሚካሄደው የሴካፋ ከ15 ዓመት በታች ውድድር ላይ ተሳታፊ የሚሆነው የኢትዮጵያ ከ15 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድንን አስመልክቶ ዛሬ ከሰዓት መግለጫ ተሰጥቷል።

በአዲስ አበባ ስታዲየም አዳራሽ በተሰጠው መግለጫ የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ሰለሞን መካ፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን የቴክኒክ እና ልማት ክፍል ሃላፊ አቶ መኮንን ኩሩ እና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን የህዝብ ግንኙነት ዳሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ በሃሩ ጥላሁን ተገኝተዋል።

ለ45 ደቂቃዎች በቆየው ጋዜጣዊ መግለጫ ስለ ብሄራዊ ቡድኑ የዝግጅት ጊዜ፣የተጨዋች አመራረጥ ሂደት እና ተያያዥ ጉዳዮች ማብራሪያ ተሰጥቷል።

በመጀመሪያ የፌደሬሽኑ የቴክኒክ እና ልማት ክፍል ኃላፊ አቶ መኮንን ኩሩ ስለ ውድድሩ ገለፃ አድርገዋል።”ከዚህ ቀደም ከ11 ዓመት በታች ቡድናችንን ወደ ቻይና ልከን ጥሩ ነገር ተመልክተናል። አሁን ደግሞ በሃገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ ተብሎ በሚታሰበው የእድሜ እርከን ቡድን አዋቅረን ወደ ኤርትራ ልንልክ ነው። በመጀመሪያ ከሴካፋ ጥሪ የደረሰን በሰኔ ወር መጨረሻ አካባቢ ነው። ይህም የተጣበበ ጊዜ እንዲፈጠር የሆነው ደግሞ የውድድሩ አዘጋጅ ኤርትራ ውድድሩን ለማከናወን ቶሎ ፈቅዳ ምላሽ ስላልሰጠች ነው። ቢሆንም ግን እኛ ዝግጅታችንን ቀደም ብለን በሃምሌ ወር መጀመሪያ ማድረግ ጀምረናል።” ብለዋል።

አቶ መኮንን በመቀጠል ተጨዋቾችን ስለመረጡበት መንገድ ማብራሪያ መስጠት ቀጥለዋል።” እንደሚታወቀው በዚህ የእድሜ እርከን የሚወዳደር ሊግ የለንም። እንደ አማራጭ የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌደሬሽን የሚያወዳድረው ውድድር ነበረ ግን ሙሉ ለሙሉ ከዛ ውድድር ብቻ የተወጣጣ ብሄራዊ ቡድን መገንባት አልፈለግንም። ስለዚህ ሁለት አማራጮችን ለመመልከት ወደናል። የመጀመሪያው የኮፓ ኮካኮላን ውድድርን መመልከት ነው።በዚህ ውድድር ጥሩ ነገር እናገኛለን ብለን አስበን ነበረ ነገር ግን ሰዎችን አሰማርተን በየውድድር ስፍራው የተመለከትነው ነገር አጥጋቢ አልነበረም። ምክንያቱም በየውድድሮቹ የነበረው የክልሎች የእድሜ ጉዳይ ችግር ነበረበት። በሁለተኝነት ደግሞ ለማድረግ የሞከርነው በየክልሉ ያሉ ተጨዋቾችን በመሰብሰብ ምልመላ ማድረግን ነው። በዚህም ከ400 በላይ ተጨዋቾችን ከየክልሎቹ ሰብስበን ተመልክተናል። ከዛም 92 ተጨዋቾችን ወደ አዲስ አበባ ጠርተን ወደ ሁለተኛ ዙር መረጣ ገብተናል። ምልመላችንንም በወጣቶችና ስፖርት አካዳሚ ለሶስት ቀናት አድርገን 20 ተጨዋቾችን ለይተናል።” ብለዋል።

የአሰልጣኞችን መረጣ በተመለከተ ሊግ አለመኖሩ እንደቸገራቸው አስረድተው ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ አካዳሚዎች በወጣቶች ላይ ለዓመታት የሰሩ አሰልጣኞች ተመልክተው ምርጫ እንዳደረጉ ተናግረዋል። አቶ መኮንን ጨምረውም ጊዜው አጭር መሆኑ ፈተና እንደሆነባቸው እና ወቅቱ ክረምት መሆኖ ለልምምድ ሜዳ እጥረት እንደዳረጋቸው አስረድተዋል።

በመቀጠል የቡድኑ አሰልጣኝ ሰለሞን መካ ስለቡድኑ የምርጫ ሂደት ማብራሪያ ሰጥቷል። ” የተጨዋቾችን ምርጫ ያደረግነው ለሶስት ቀን ነው። አርብ ቅዳሜ እና እሁድ ካሉን 92 ተጨዋቾች 27 ተጨዋቾችን መርጠናል። 7 ተጨዋቾችን የመረጥነው ደግሞ ድንገተኛ ነገር ከተፈጠረ ብለን ነው። ነገር ግን ከሰኞ በኋላ የፓስፖርት ጉዳይ ማለቅ ስለነበረበት ሰኞ 20 ተጨዋቾችን ለይተናል።” ብለዋል።

አሰልጣኙ ማብራሪያቸውን ቀጥለው ስላደረጉት አጭር የዝግጅት ጊዜ የሚከተለውን ብለዋል።” ካለው የጊዜ አጭርነት አንፃር መደበኛ ልምምድ ያደረግነው ለሶስት ቀናት ብቻ ነው። ሰኞ፣ እረቡ እና ዛሬ ልምምዳችንን በጥሩ ሁኔታ ሰርተናል። ማክሰኞ ልምምድ ያልሰራነው የፓስፖርት ጉዳይ ስለነበረብን ነው። ከሞላ ጎደል ግን ትኩረት አድርገን የሰራነው የውህደት(organisation) ስራን ነው። ተጨዋቾቹ ከዚህ ቀደም ስለማይተዋወቁ እነሱን እንደ ቡድን ማዋሃድ ነበረብን። ስለዚህ ባለን ጊዜ ልጆቹን ሜዳ ላይ ለማግባባት ሞክረናል።” ብለዋል።

በመቀጠል በቦታው ከተገኙ የሚዲያ አካላት ስለ ቡድኑ ግብ፣ ስለተመረጡት ተጨዋቾች እድሜ ትክክለኛነት፣ ስለ ቡድኑ ቀጣይ እጣ ፋንታ እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ጥያቄዎች ተነስተው ማብራሪያ ተሰጥቷል። ቡድኑ በዋነኝነት ከውድድሩ ልምድ እንዲያገኝ እንደሚጓዝ የገለፁት አቶ መኮንን ውድድሩ የታዳጊዎች እንደመሆኑ ውጤት መታየት እንደሌለበት ጠቁመዋል። አቶ መኮንን ስለ ቡድኑ ቀጣይ እጣ ፋንታ ለተጠየቁት ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ ቡድኑ ከውድድሩ በኋላ እንደማይበተን እና ተጨዋቾቹ በአካዳሚዎች ተይዘው ቀጣይነት ያለው ስልጠና እንዲያገኝ እንደሚደረግ ገልፀዋል።

በመጨረሻም የተጨዋቾችን የእድሜ ትክክለኝነት በተመለከተ ለቀረበ ጥያቄ አቶ መኮንን ምላሽ ሰጥተዋል።” እድሜን በተመለከተ ምልከታ ነው። ሌላ ምንም ነገር የለም። የኤም አር አይ ምርመራ አልተደረገም። ሴካፋም ያለን ነገር የለም። በምልከታ ግን ተጨዋቾችን መርጠናል። አሁን ግን ከሌላው ጊዜ በተለየ እድሜ ላይ የተሻለ ነገር እንዳለ ላረጋግጥላችሁ እወዳለው።” ብለዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡