ከኢትዮጵያ ቡና ጋር የተለያየው ክሪዚስቶም ንታምቢ ለአዲስ አዳጊው የሀገሩ ፕሪምየር ሊግ ክለብ ፊርማውን አኑሯል።
በ2009 በደቡብ አፍሪካ ሁለተኛ ዲቪዚዮን ይወዳደር ከነበረው ቫዝኮ ደጋማ ክለብ ወደ ጅማ አባ ቡና በማቅናት ጥሩ ጊዜ ያሳለፈው ንታምቢ ቡድኑን ለአንድ አመት አገልግሎ ወደ ኢትዮጵያ ቡና ማምራቱ ይታወሳል። ተጨዋቹም በኢትዮጵያ ቡና በሁለት ቦታዎች (በተከላካይ አማካይ እና በተከላካይ) በመሰለፍ ለሁለት ዓመታት ጥሩ ግልጋሎት አበርክቷል።
ዩጋንዳዊው ተጨዋች ዳግም ወደ ሃገሩ ሊግ በማቅናት ለዋኪሶ ጂያንትስ ለመጫወት ዛሬ ፊርማውን አኑሯል። ዋኪሶ ጂያንትስ በዘንድሮ የዩጋንዳ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያ ተሳትፎ የሚያደርግ ሲሆን 13 አዳዲስ ተጨዋቾችም ወደ ቡድኑ ቀላቅሏል። ንታምቢን ጨምሮ ቡድኑ ካስፈረማቸው 13 ተጨዋቾች መካከል በ1999 ለቅዱስ ጊዮርጊስ የተጫወተው ጂዮፍሬ ሴሬንኩማ ይገኝበታል።
ክሪዚስቶም ንታምቢ ግብፅ አዘጋጅታ በነበረው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ለመሳተፍ በብሄራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ሴባስቲያን ዴሳብር ተመርጦ በመጨረሻ ስብስብ ሳይካትት መቅረቱ ይታወሳል።
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡