ከ17 ዓመት በታች የሴቶች ብሄራዊ ቡድናችን ወደተከታዩ የማጣርያ ዙር ሳያልፍ ቀረ

የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች የሴቶች ብሄራዊ ብድኑ በካሜሮን አቻው በመለያ ምት ተሸንፎ ከዓለም ዋንጫው ማጣሪ ውጪ ሆኗል፡፡

ከሁለት ሳምንት በፊት ብሄራዊ ብድኑ ዱዋላ ላይ 2-1 በሆነ ጠባብ ውጤት የተሸነፈ ሲሆን በዛሬው ጨዋታ በሜዳው እና ደጋፊው ፊት 2-1 ማሸነፍ ቢችልም በመለያያ ምት 5-4 ተሸንፎ ዮርዳኖስ ከምታዘጋጀው የዓለም ዋንጫ ለማለፍ የነበረው ህልም ተጨናግፏል፡፡

ኢትዮጵያ በጨዋታው መጀመሪያ 30 ደቂቃዎች ተጋጣሚዋ ላይ ከፍተኛ ጫና አሳድራች፡፡ ትደግ ፍስሃ በ9ኛው ደቂቃ የግል ብቃቷን ተጠቅማ ኢትዮጵያ በአጠቃላይ ውጤት አቻ ስታደርግ በ18ኛው ደቂቃ የምስራች ላቀው ሁለተኛው ግብ አክላ 2-0 በሆነ ውጤት ለዕረፍት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ብድን በእጅጉ ተዳክሞ የታየ ሲሆን በተደጋጋሚ በካሜሮን ተጨዋቾች ሲፈተን ተስተውሏል፡፡ ካሜሮኖች ጨዋታው ሊጠናቀቅ 3 ደቂቃ ሲቀረው በአጠቃላይ ውጤት አቻ ያደረገቻቸውን ግብ አሌክሳንደራ ታኮንዳ አስቆጥራለች፡፡

አላፊውን ቡድን ለመለየት በተሰጠው መለያ ምት ካሜሮን 5-4 በማሸነፍ ወደ መጨረሻው የማጣሪያ ዙር አልፋለች፡፡ ካሜሮን ከግብፅ እና ጁቡቲ አሸናፊ የምትገናኝ ይሆናል፡፡ ግብፅ ጅቡቲን በመጀመሪያው ዙር 6-0 በሆነ ሰፊ ውጤት አሸንፋለች፡፡

IMG_0183

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ አስተያየታቸውን የሰጡት ከ17 ዓመት ብሄራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ አስራት አባተ ልምድ የሌለው ቡድን መሆኑ እንደችግር አንስተዋል፡፡ “ቡድኑ ልምድ የለውም፡፡ ጨዋታውን በመለያ ምት መሸነፍ ችለናል፡፡ መጥፎ የሚባል ውጤት አይደለም፡፡ ከውድድር መውጣቱ ራሱን የቻለ አሉታዊ ጎን አለው ቢሆንም አቅም ያላቸውን ተጨዋቾች ያየንበት ነበር፡፡ በሁለተኛው አጋማሽ አጥቅተን ጨዋታው ለመጨረስ ተነጋግረን ገብተን ነበር፡፡ ሆኖም ግን ውጤትን ከመፈለግ የተነሳ አፈግፍጎ የመጫወት ነገር ነበር፡፡ ይህ ደግሞ ከልምድ ማነስ የመጣ ነው፡፡” አሰልጣኙ አክለው ደጋፊው በተደጋጋሚ ሲሰነዝርባቸው የነበረውን ተቃውሞ እንዳልወደዱት ጠቁመዋል፡፡ 

“ለነዚህ ልጆች መምጣት ከፍተኛ መስዋትነት ከፍያለው፡፡ በውድድሩም ላይ ከፍተኛ የሆነ ትግል አድርገናል፡፡ ነገር ግን እንዳያችሁት ተመልካቹ በባለሞያው ደስተኛ አይደለም፡፡ ያ ደግሞ ለኔ ደስታ አልሰጠኝም፡፡ መመስገን ያለበት ተጫዋቾቹ አና ቡድኑ ናቸው እኔም ብሆን መመስገን ነበረብኝ፡፡ ስለዚህ ከዛሬ በኃላ የትኛውንም ብሄራዊ ብድን የማሰልጠን ፍላጎት አይኖረኝም፡፡” ብለዋል፡፡

IMG_0181

 

 

የካሜሮን አሰልጣኝ ሚንክሪዮ ቢርዊ በበኩላቸው የስነ-ልቦና ጥንካሬ ለአሸናፊነት እንዳበቃቸው ተናግረዋል፡፡ “ጥሩ ጨዋታ ነበረ፡፡ ሁለት ጥሩ እና ጠንካራ ብድኖችን ተመልክተናል፡፡ የኢትዮጵያ ብድን ጥሩ የቴክኒክ ችሎታ ያላቸውን ተጫዋቾች ይዟል፡፡ ተጫዋቾቼ በስነ-ልቦናው ረገድ ጠንካራ መሆናቸው ለአሸናፊነት አብቅቶናል፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽ ችግር ነበረብን፡፡ በሁለተኛው አጋማሽ ተሻሽለን ቀርበን ውጤቱን መለወጥ ችለናል፡፡” ብለዋል፡፡

ያጋሩ