ወደ ጊኒው ቻምፒዮን ሆሮያ ለማምራት ተስማምቶ የነበረው ከነዓን ማርክነህ ዝውውሩን ለማጠናቀቅ ዕክል ገጥሞታል።
ባለፈው ወር አጋማሽ የአዳማ ከተማው ተስፈኛ አማካይ ከነዓን ማርክነህ ወደ ጊኒው ሻምፒዮን ሆሮያ ለመቀላቀል መስማማቱ መግለፃችን ይታወሳል። አሁን እየወጡ ባሉት መረጃዎች ግን የዝውውር ሂደቱ ቢጠናቀቀም በዝውውር መስኮት መዘጋት ምክንያት ስሙ በጊኒ እግርኳስ ፌዴሬሽን ተሞልቶ ወደ ካፍ አለመላኩ ታውቋል። በዚህም ምክንያት ስሙ በቻምፒየንስ ሊግ ዝርዝር ውስጥ ሳይካተት ቀርቷል።
የመጀመርያው የውል ስምምነት (ከታች በፎቶ የሚገኘው) ዕክል ከገጠመው በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ ከጊኒው ክለብ ሌላ የስምምነት ጥያቄ የቀረበለት ተጫዋቹ የቡድኑን የውል ጥያቄ ውድቅ አድርጎታል። ክለቡ ያቀረበው የውል ጥያቄ የሃገሪቱ ሊግ እስኪጀመር ባሉት አራት ወራት ከቡድኑ ጋር ልምምድ እየሰራ እንዲቆይና ውድድሩ ሲጀምር ከቡድኑ ጋር ተቀላቅሎ እንደሚጫወት በማሰብ እስከዛ ድረስ ግን አስቀድመው በመጀመርያው ስምምነት ላይ የተካተቱ ጥቅማጥቅሞች በሙሉ እንደማይከፈለው እና መጫወት ከሚጀምርበት ጊዜ ጀምሮ ግን ክፍያ እንደሚፈፀምለት የሚገልፅ አዲስ ውል ልከውለታል። ከነዓን በበኩሉ ሊጉ እስኪጀምር ድረስ ካለደሞዝ ከቡድኑ ጋር ቆይታ ለማድረግ እንደሚቸገር በመግለፅ አስቀድሞ የተፈፀመው ውል ተግባራዊ እንዲደረግ ለክለቡ ምላሽ የሰጠ ሲሆን ክለቡም እስካሁን ድረስ ለከነዓን ጥያቄ ምላሽ አልሰጠም።
የክለቡ ምላሽ መዘግየቱ ምናልባትም ከነዓን ወደ ሆሮያ የሚያደርገው ጉዞ ሊሰናከል እንደሚችል ፍንጭ ሰጥቷል።
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡