በ2019/20 የካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ቅድመ ማጣርያ ወደ ዳሬሰላም አምርቶ የመልስ ጨዋታውን ያደረገው ፋሲል ከነማ በአዛም 3-1 (በድምር ውጤት 3-2) ተሸንፎ ከውድድሩ ውጪ ሆኗል።
10:00 ላይ በአዛም ኮምፕሌክስ በተደረገው በዚህ ጨዋታ ፋሲል ከነማ ባህር ዳር ላይ 1-0 ካሸነፈበት ጨዋታ አሰላለፍ በጉዳት ወደ ስፍራው ባልተጓዘው በዛብህ መለዮ ምትክ ሰለሞን ሀብቴን ሲጠቀሙ በመጀመርያው ጨዋታ በጉዳት ምክንያት በጊዜ ተቀይሮ የወጣው ሚኬል ሳማኬም በአሰላለፍ ውስጥ ተካቶ ጨዋታውን ጀምሯል።
ግብ በማስቆጠር ቅድሚያውን የያዙት ባለሜዳዎቹ ሲሆኑ በ23ኛው ደቂቃ ጋናዊው አጥቂ ሪቻርድ ጆዲ ቡድኑን በድምር ውጤት ያስተካከለች ጎል አስቆጥሯል። አጥቂው በ31ኛው ደቂቃ ላይም ሁለተኛውን ጎል አክሎ የአዛምን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ ቢያደርግም ከአምስት ደቂቃዎች በኋላ ፋሲሎች ወደ ጨዋታው የመለሰናቸውና በድምር ውጤትም የማለፍ እድል የሚሰጣቸውን ጎል በሙጂብ ቃሲም አማካንነት አስቆጥረው የመጀመርያው አጋማሽ በአዛም 2-1 መሪነት ተገባዷል።
ከእረፍት መልስ ፋሲሎች የያዙትን ውጤት የማስጠበቅ አላማ ይዘው ወደ ሜዳ ቢገቡም በ58ኛው ደቂቃ ኦብሬይ ቺርዋ ያስቆጠራት ጎል የፋሲልን ተስፋ ያጨለመች ሦስተኛ ጎል ሆና ተመዝግባለች። ጨዋታውም ተጨማሪ ጎል ሳይቆጠርበት በአዛም 3-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ውጤቱን ተከትሎ የመጀመርያ አህጉራዊ የክለብ ውድድር ተሳትፎውን ያደረገው ፋሲል ከነማ በድምር ውጤት 3-2 ተሸንፎ ከቅድመ ማጣርያው ተሰናብቷል።
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡