ባህር ዳር ከተማ የተጫዋቾቹን ውል ማደስ ጀምሯል

ፋሲል ተካልኝን በአሰልጣኝነት የሾሙት የጣና ሞገዶች ወደ ዝውውር መስኮቱ ገብተው አዳዲስ ተጨዋቾችን ከማስፈረማቸው ቀደም ብለው የነባር ተጨዋቾቹን ውል ማደስ ጀምሯል።

የመጀመሪያው ውሉን ያደሰ ተጨዋች አምበሉ ደረጄ መንግስቱ ነው። የቀድሞ የሐረር ቢራ፣ ዳሽን ቢራ እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተጨዋች በባህር ዳር ከተማ በአምበልነት ለአመታት ግልጋሎት የሰጠ ሲሆን አሁንም በጣናው ሞገዶቹ ቤት ለመቆየት ተስማምቷል። አምና ከፋሲል ከነማ ወደ ባህር ዳር በመምጣት ድንቅ ጊዜ ያሳለፈው ፍቅረ ሚካኤል ዓለሙ ሁለተኛው ውሉን ያደሰ ተጨዋች ነው። የአማካይ መስመር ተጨዋቹ ከባህር ዳር ከተማ በፊት በሴንትራል ዩኒቨርስቲ፣ በአውስኮድ እና ፋሲል ከነማ መጫወት የቻለ ሲሆን በቀጣይ ለሁለት ዓመት ከባህር ዳሮች ጋር ለመቀጠል ፊርማውን አኑሯል።

ከሁለቱ የቡድኑ ወሳኝ ተጨዋቾች በተጨማሪ ዓምና ወጥ አቋም ያሳዩት የተከላካይ መስመር ተጨዋቹ አቤል ውዱ እና የአማካይ መስመር ተጨዋቹ ዳንኤል ኃይሉን ጨምሮ ዳግማዊ ሙሉጌታ፣ ዜናው ፈረደ፣ ሄኖክ አቻምየለህ እና ሥነ-ጊዮርጊስን እንዳስፈረሙ ለሶከር ኢትዮጵያ የገለፁት ባህር ዳሮች ከሁለተኛ ቡድናቸው ኃይሉ የተባለ ተጨዋች ማሳደጋቸውን ጨምረው ገልፀዋል።

እስካሁን ምንም ተጨዋች ወደ ቡድናቸው ያላመጡት ባህር ዳሮች በቀጣይ ቀናት አዳዲስ ተጨዋቾችን ወደ ቡድናቸው በማምጣት ለማስፈረም እንቅስቃሴ መጀመራቸው ተሰምቷል። ባህር ዳሮች ትላንት እና ዛሬ ውላቸውን ካደሱላቸው ስምንት ተጨዋቾች በተጨማሪ በቀጣይ ሌሎች ወሳኝ ተጨዋቾቻቸውን በቡድናቸው ለማቆየት ድርድር ላይ መሆናቸውን ገልፀዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡