አስቀድመው የአራት ተጫዋቾችን ዝውውር የፈፀሙት ባህር ዳሮች በዛሬው ዕለት ወጣቱ ግብ ጠባቂ ፅዮን መርዕድን ወደ ክለባቸው ቀላቅለዋል፡፡
ከአርባ ምንጭ ታዳጊ ቡድን የተገኘው ፅዮን ባለፉት ሦስት ዓመታት በአርባ ምንጭ ዋናው ቡድን ውስጥ ቆይታን ያደረገ ሲሆን ከ2010 የውድድር ዘመን ጀምሮ በቋሚነት በመጫወት ተስፈኛ ግብ ጠባቂነቱን አሳይቷል። ለወጣት እና ዋናው ብሔራዊ ቡድን መመረጥ የቻለው ይህ ግብ ጠባቂ ከሳምንታት በፊት መቐለን ለመቀላቀል የተስማማ ቢሆንም በአንዳንድ ጉዳዮች መስማማት ሳይችል በመቅረቱ ተለያይቶ በሁለት ዓመት ውል ማረፊያውን የአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ክለብ ባህር ዳር ሆኗል፡፡ ክለቡን የለቀቀው ምንተስኖት አሎን ቦታ ይሸፍናል ተብሎም ይጠበቃል።
ከሰሞኑ በንቃት በዝውውር መስኮቱ ያሉት ውሀ ሰማያዊ ለባሾቹ የአጥቂ ስፍራ ተጫዋቹን ፍቃዱ ወርቁን ውል ለተጨማሪ ሁለት ዓመት አራዝመዋል፡፡
© ሶከር ኢትዮጵያ