“ቡና ደሜ ነው ” በሚል መሪ ቃል ለ4ኛ ጊዜ የተካሄደው የኢትዮጵያ ቡና የቤተሰብ ሩጫ ከ40 ሺህ በላይ ተሳታፊዎችን አሳትፎ መነሻውን እና መድረሻውን መስቀል አደባባይ በማድረቅ በደማቅ ሁኔታ ተጠናቀቀ።
በመስቀል አደባባይ ሲካሄድ የመጀመርያው በሆነው የኢትዮጵያ ቡና 4ኛው የቤተሰብ ሩጫ ጥሪ የተደረገላቸው የክብር እንግዶች የአዲስ አበባ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ዮናስ አረጋይ ፣ የኦሊምፒክ ኮሚቴ ም/ፕሬዝደንት ብርቅዬዋ አትሌት ደራርቱ ቱሉ፣ የአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝደንት ኃይለየሱስ ፍሰሀ (ኢ/ር)፣ የኢትዮጵያ ቡና ክለብ ፕሬዝደንት መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ እና የተለያዩ ባለሀብቶች፣ ታዋቂ አርቲስቶች በሩጫው ሥነ ስርዓት ላይ ታድመዋል።
የኢትዮጵያ ቡና ምክትል የቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ይስማሸዋ በመርሐ ግብሩ ማስጀመርያ ላይ ባደረጉት ንግግር የኢትዮጵያ ቡና የቤተሰብ ሩጫ ከዓመት ዓመት በተሳታፊ ቁጥር በደጋፊዎች ዘንድም ተወዳጅነቱ እየጨመረ መምጣቱን ገልፀው በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ውስጥ ቁጥሩን አሁን ካለው አርባ ሺህ ተሳታፊ ወደ መቶ ሺህ ከዛም በላይ ከፍ በማድረግ በዓለም ድንቃድንቅ መዝገብ በሪከርድነት እንደሚመዘገብ ለደጋፊዎቹ ገልፀዋል። ሩጫው ከመቼውም ጌዜ በደመቀ ሁኔታ ለመጀመርያ ጊዜ በመስቀል አደባባይ እንዲካሄድ ለፈቀዱት እና ለኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች አመራር በሙሉ ምስጋና አቅርበዋል።
ከሩጫው መጀመር አስቀድሞ የ2012 የኢትዮጵያ ቡና ዋና አሰልጣኝ በመሆን የተሾመውና በቅሩቡ ከሚኖርበት አሜሪካ ወደ ትውልድ ሀገሩ የተመለሰው አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ በመስቀል አደባባይ ከሚገኙት የክለቡ ደጋፊዎች ጋር ትውውቅ አድርጓል።
ጀግናዋ አትሌት ደራርቱ ቱሉ እና በዕለቱ በተገኙት የክብር እንግዶች በይፋ የተጀመረው የኢትዮጵያ ቡና የቤተሰብ ሩጫ መነሻውን መስቀል አደባባይ አድርጎ መስቀል አደባባይ እስኪጠናቀቅ ድረስ በየመንገዱ የተለያዩ ክለባቸውን የሚያወድሱ ፣ ዜማዎች ግጥሞች፣ የተለያዩ አዝናኝ መልክቶችን በማስተላለፍ እና የተለያዮ ትዕሪቶችን በኅብረት በማሳየት በደመቀ ሁኔታ ተጀምሮ በሠላም ተጠናቋል።
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡