የአሰልጣኞች አሰተያየት | ኢትዮጵያ 1-1 ካሜሩን

በቶኪዮ ኦሊምፒክ የማጣሪያ ጨዋታ ሉሲዎቹ ካሜሩንን በባህር ዳር ኢንተርናሽናል ስታድየም አስተናግደው 1-1 ከተለያዩ በኋላ የሁለቱ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኞች አስተያት ሰጥተዋል።

“ጨዋታው አልቋል ብለን አናስብም” ሠላም ዘርዓይ

ስለ ጨዋታው

ጨዋታው በሜዳችን ቢሆንም ከባድ እና አስቸጋሪ ነበር። በመጀመሪያው አጋማሽ ቡድኑን አክብዶ ከማየት አንፃር በእንቅስቃሴ ውስጥ በራስ መተማመናችንን አጥተን ነበር። በሁለተኛው አጋማሽ ደግሞ ወዲያው እነሱ ማጥቃት በመጀመራቸው ምክንያት ቡድናችን ቅርፁን አጥቶ ነበር፤ ከዛ ግብ ተቆጠረብን። ግብ ከተቆጠረብን በኋላ በቀየርናቸው ተጫዋቾች ምክንያት ውጤቱን ለማስመለስ ሞክረናል። ማሸነፍ ባንችልም በአጠቃላይ ውጤቱ ጥሩ ነበር ።

ስለ ተጫዋቾች የአካል ብቃት ችግር

የአካል ብቃት ችግር እንዳለ እኔም አምናለሁ። አንደኛ የተሰጠን የዝግጅት ጊዜ ትንሽ ነው። ወደ 17 ቀን አካበቢ ብቻ ነው የተዘጋጀነው። ተጫዋቾቹ ደግሞ ከሁለት ወር በላይ እረፍት ላይ ስለነበሩ ከውድድር ከራቁ ረጅም ጊዜያቸው ነው። ስለዚህ ችግሩ በዚህ ምክንያት የመጣ ነው። በጊዜ ሂደት የሚስተካከልም ነው።

ስለመልሱ ጨዋታ

እንግዲህ ጨዋታው አልቋል ብለን አናስብም። ግማሹ ጨዋታ አልቋል። በዚህ ሁኔታ እዛ ደግሞ ስንሄድ ከዚህ የበለጠ ከባድ ጨዋታ እንደሚጠብቀን እናውቃለን። ለመልሱ ጨዋታ በቀሩት ጊዚያት ተዘጋጅተን፤ ድክመታችን ላይ ሰርተን ውጤት ለመያዝ እንሞክራለን ።

ስለ ተጋጣሚ

የካሜሩን ቡድን የሚናቅ አይደለም። አሁን በምናየው እንቅስቃሴ ብቻ ሳይሆን ትልቅ እና የሚከበር ቡድን ነው። ነገር ግን አሁን በምናየው የኛ ተጫዋቾች የልምድ ማነስ እና የራስ መተማመን ችግር ባይሆን ኖሮ ውጤቱን መያዝ እንችል ነበር።

የተጫዋቾች ቅያሪ መዘግየት

ቅያሪዎች ቁማሮች ናቸው። አንዳንድ ጊዜ ሊሳኩ ይችላሉ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ አይሳኩም። ስለዚህ አሁን ያገጠመን ትክክለኛ ቅያሪ ነው ማለት ነው። እኔ እንደዛ ነው የማምነው።

“በልምድ በኩል እኛ የተሻልን ነበርን” አላይን ጄውምፋ

ስለ ጨዋታው

ኢትዮጵያ ጥሩ ጨዋታ ብታሳይም የኛ ተጫዋቾች ልምድ ያላቸው ናቸው። በዛ እኛ የተሻልን ነበርን። ሜዳችን ላይ ለምናደርገው የመልስ ጨዋታ ዝግጅታችን እንቀጥላለን። ጨዋታ ጨዋታ ነው፤ ስለዚህ በሚገባ መዘጋጀት አለብን። ካሜሩን ወደ ቀጣይ ዙር ማለፍ ትችላለች ።

የመልስ ጨዋታ

ጥሩ ጨዋታ ይሆናል ብዬ አስባለሁ። የተሻለ ስብስብ ይዘን እንቀርባለን ብዬ አስባለሁ።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡