በክቡር ይድነቃቸው መታሰቢያ ውድድር ለፍፃሜ የደረሱ ቡድኖች ታውቀዋል

በ15 ዓመት በታች ታዳጊዎች መካከል እየተካሄደ በሚገኘው 14ኛው የክቡር ይድነቃቸው ተሰማ የመታሰቢያ ውድድር ዛሬ የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታዎች ተካሂደው ኤንፓ እና አብዲ ቦሩ ለፍፃሜ የሚያበቃቸውን ድል አስመዝግበዋል።

03:00 ጀሞ በሚገኘው ዶንቦስኮ ሜዳ በጀመረው ጫጫ ከአብዲ ቦሩ ያገናኘው ጨዋታ በአብዲ ቦሩ የበላይነት በመውሰድ 3-0 አሸንፏል። ጥሩ ክህሎት ባላቸው ታዳጊዎች የተዋቀረው አብዲ ቦሩዎች በሙሉ ብልጫ ነው ማሸነፍ ሲችሉ በመጀመርያው አጋማሽም ብሩክ ፍቃዱ ባስቆጠረው አንድ ጎል እየመሩ ነበር እረፍት የወጡት። ከደብረ ብርሃን ድረስ በመምጣት የውድድሩ ተጋባዥ የሆኑት ጫጫዎች በውድድሩ ላይ ከነበረው ጥሩ እንቅስቃሴ ዛሬ ደከም ብለው ቢታዩም ታዳጊው አምሳለ ሽመልስ በግሉ በዚህ ዕድሜው የሚያደርገው እንቅስቃሴ አስገራሚ ነበር።

ብልጫ ወስደው መጫወታቸውን በሁለተኛው አጋማሽ የቀጠሉት አብዲ ቦሩዎች የመጀመርያውን ጎል ባስቆጠረው ብሩክ ፍቃዱ አማካኝነት ከርቀት በተመታ ግሩም ኳስ ሁለተኛ ጎል አስቆጥረዋል። እንደ ቡድን ተጫውተው ጎል ለማስቆጠር የተቸገሩት ጫጫዎች ወደ ጨዋታው የሚመልሳቸውን ጥረት ሳያደርጉ በመጨረሻም በሐብታሙ ጉልላት ሦስተኛ ጎል አስቆጥሮ ጨዋታው በአብዲ ቦሩ የበላይነት 3-0 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

በአብዲ ቦሩ ቡድን ውስጥ ጎል በማስቆጠርም ሆነ በእንቅስቃሴው የሚያድግ ተስፋ ሰጪ ነገር የተመለከትንበት አስር ቁጥር ለባሹ ብሩክ ፍቃዱ ጥሩ መንቀሳቀስ የቻለ ሲሆን በተመሳሳይ ከረጅም ርቀት አቋርጠው እንደመምጣታቸው ለፍፃሜ ባለመድረሳቸው ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ በቁጭት ሲያለቅሱ ከተመለከትናቸው የጫጫ ቡድን ውስጥ እጅግ አስገራሚ የተፈጥሮ አቅም እንዳለው በየጨዋታዎቹ ያስመሰከረው አምሳለ ሽመልስ ወደ ፊት ጥሩ ተጫዋች እንደሚሆን ማሳየት ችሏል።

04:00 በቀጠለው ሌላኛው የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ ኤንፓ ከአዳማ ብሩህ ተስፋ አገናኝቶ ጥሩ ፉክክር አስመልክቶን ጨዋታው በኤንፖ 3-2 አሸናፊነት ተጠናቋል። ጎል በማስቆጠር ቀዳሚ የሆኑት እንግዶቹ አዳማዎች ነበሩ። በየትኛውም ቦታ ያገኘውን ኳስ ኢላማውን ጠብቆ ወደ ጎል በመምታት በውድድሩ ላይ በከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነት እየተፉካከረ የሚገኘው የስሙ መገጣጠም ሆነ የአጥቂነት ባህሪው ከመቐለ ሰባ እንደርታው አጥቂ ጋር የሚመሳሰለው የአዳማዎቹ ታዳጊ አጥቂ አማኑኤል ገ/ሚካኤል ከርቀት ኳሱን መጥኖ ወደ ጎል በመምታት ባስቆጠረው ጎል መምራት ችለው ነበር።

ብዙም ሳይቆይ ኤንፖዎች ከቅጣት ምት አምሐ ዳምጤ አቻ የምታደርጋቸውን ጎል አስቆጥሯል። ከእረፍት መልስ ተመጣጣኝ ፉክክር ያድጉት ሁለቱ ቡድኖች ቀጥለው በቆመ ኳስ አጠቃቀማቸው የተሻሉ የነበሩት ኤንፓዎች ለራሱም ለቡድኑም ሁለተኛ ጎል በአምሐ ዳምጤ አማካኝነት የቅጣት ምት ጎል አስቆጥረዋል። ኤንፓዎች ያገኟቸውን የቅጣት ምት ኳሶች በአስገራሚ አጨራረስ በመቀየር ውጤታማ መሆናቸው ጠቅሟቸው አምሐ ዳምጤ ለራሱ ሐት-ትሪክ የሰራበትን ለቡድኑም ሦስተኛ ጎል ከቅጣት ምት አስቆጥሮ የግብ መጠናቸውን ከፍ አድርጓል። የጨዋታው መጠናቀቂያ ላይ ውጤቱን መቀየር ባይችልም በአዳማዎች በኩል እዮብ ይገርማል ሁለተኛ ጎል አስቆጥሮ ጨዋታው በኤንፓ 3-2 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ቅዳሜ ነሐሴ 25 ቀን 2011

03:00 | ጫጫ ከ አዳማ ብሩህ ተስፋ ለደረጃ
04:00 | አብዲ ቦሩ ከ ኤንፓ ለዋንጫ


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡