“ቁጭ ብለን ማሰብ አለብን ” አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ

በ2012 የውድድር ዘመን ኢትዮጵያ ቡና ፊቱን ወደ ኢትዮጵያዊ አሰልጣኝ አዙሮ የቀድሞ ተጫዋቹና አሰልጣኝ የነበረው ካሳዬ አራጌን ዳግም ከረጅም ዓመታት በኋላ ቡድኑን እንዲያሰለጥን በመፍቀዱ አሰልጣኙ በቅርቡ አዲስ አበባ ገብቷል። ምንም እንኳን የክለቡ ዋና አሰልጣኝ መሆኑ በይፋ ባይረጋገጥም ከቀናት በፊትም በ4ኛ የኢትዮጵያ ቡና የቤተሰብ ሩጫ ላይ በመገኘት ከሚወዱት ደጋፊዎች ጋር ትውውቅ አድርጓል። ሶከር ኢትዮጵያም በዚህ አጋጣሚ ከአሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ጋር አጭር አድርጋ እንዲህ አሰናድታ አቅርባዋለች።

ከአስራ ስድስት ዓመታት በፊት ኢትዮጵያ ቡናን በዋና አሰልጣኝነት ይዘህ ብዙም አልቆየህም። አሁን ዳግመኛ ከረጅም ዓመታት በኃላ በድጋሚ ቡድኑን ለመረከብ ተመልሰሀል። ያንጊዜ አሁን ስታስበው መስራት እየቻልኩ በቂ ጊዜ ሊሰጠኝ ባለመቻሉ በመሆኑ የባከኑ ዓመታቶች አሉ ትላለህ ?

ምንም ጥርጥር የለውም በማንኛውም ሁኔታ አንድን ነገር ለመስራት ረጅም ጊዜ ስታገኝ ያቀድከውን ለማሳካት ትችላለለህ። ምንም ጥርጥር የለውም በጣም የባከኑ ብዙ ጊዜያቶች አሉ።

ዳግመኛ ወደ ኢትዮጵያ ቡና ስትመጣ ከዚህ ቀደም የነበሩ ተመሳሳይ ችግሮች እንዳይፈጠሩ በምን ስምምነት ነው ተነጋግረህ የመጣኸው?

ያለቀ ነገር የለም፤ ገና ሂደት ላይ ያሉ ነገሮች ናቸው። ሁሉም ነገር ተጠናቆ ሲያልቅ የምገልፅልህ ይሆናል። አሁን ምንም የምለው ነገር የለም።

የክለቡ አሰልጣኝ ከመሆንህ ጋር ተያይዞ ገና ያልተጠናቀቀ ነገር አለ?

አዎ። ከመቶ ሰማንያ ፐርሰንት ተጠናቋል ማለት ይቻላል። ሆኖም ወደ ፊት ሁሉ ነገር ሲጠናቀቅ ሰፊ ማብራሪያ እና የስምምነታችን አካል ምን እንድሆነ ብነግርህ የተሻለ ነው።

የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊ አንተ እንድትመጣ ከፍተኛውን ሚና ተወጥቷል። በተለያዩ መንገዶች ለክለቡ አመራሮች አንተ እንድትመጣ ጥያቄ ያቀርብ ነበር። ዛሬ ተሳክቶ ከረጅም ዓመት በኃላ ዛሬ ከደጋፊው ጋር በዚህ የሩጫ ቀን ትውውቅ አድርገሀል። ምን ዓይነት ስሜት ፈጠረብህ?

ተጫዋችም አሰልጣኝ በሆንኩበት ዓመታት አሁን የምትመለከተው ደጋፊ መንፈሱ አንድ ዓይነት ነው። ከፊት ከነበረው የአሁኑ ቁጥሩ መጨመሩ ካልሆነ በቀር አንድ ዓይነት የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊ ነው። ሁልጊዜ ደጋፊው ላይ የምታየው ለቡድኑ ራስን በመስጠት ነው ቡድናቸውን የሚደግፉት፤ ያነገር አንድ ያደርጋቸዋል። እኔ በፊት ከማየው ምንም የተለወጠ ነገር የለም እንዳለ ነው። የቁጥሩ መጨመር ግን የሚታይ ነው።

የቀጣይ የሊግ ውድድሮች የሚጀምሩበት ጊዜ እየተቃረበ ይገኛል። ክለቦች በከፍተኛ ሁኔታ በዝውውሩ ሂደት እየተሳተፉ ነው። ከዚህ አንፃር ኢትዮጵያ ቡና ዘግይቷል ማለት ይቻላል። ወደ ሀገር ቤት ከመጣህ በኃላ በዝውውሩ ላይ ምን ዓይነት እንቅስቃሴ እያደረግክ ነው?

ለእኔ አጨዋወት ይሆናሉ ብዬ ያሰብኳቸው ተጫዋቾች ስም ዝርዝር ይዣለው። ሆኖም እንደ ልብ ወደ ስራ ገብተህ የምትፈልጋቸውን ተጫዋቾች ለመውሰድ አሁን በቅርብ የተፈጠረው የተጫዋቾች የዝውውር ጣርያ ተጫዋቹን ነፃ ሆኖ በአንድ ነገር ላይ ተረጋግቶ ይሄ ነው የሚሻለኝ ብሎ እንዳይወስን አድርጎታል። የተለያዩ መረጃዎች ከተለያዩ ሰዎች ስለሚመጡ በአንድ ነገር ላይ አቋም ይዞ ይህ ነው የሚገባኝ በማለት እንዳይወስን እና ስህተትም እንዳይሰራ በመስጋትም ይመስለኛል ወደ ዝውውሩ መግባት አልቻሉም። ይህ ደግሞ በእኛ ስራ ላይ ችግር ፈጥሯል። ተስፋ አደርጋለው በሂደት ችግሮቹ እየቀለሉ እኛም የምንፈልጋቸውን ተጫዋቾች ወደ ማስፈረሙ እንገባለን።

በቀጣይ ዓመት ደጋፊው ከአንተ ምን ይጠብቅ ?

እኔ እንግዲህ በፊትም የማስበው ፣ አሁንም የማስበው ኢትዮጵያ ቡና የራሱ የሆነ ነገር እንዲኖረው እፈልጋለው። በተለይ ለቡድኑ እጫወትባቸው በነበሩ የመጀመርያዎቹ ዓመታት ብዙ የምታስተውለው ነገር የለም። ዝም ብሎ ከመጫወት በቀር የምታስተውላቸው ነገሮች የሉም። ከተወሰኑ ዓመታት በኃላ በተጫዋችነት ዘመን አሰልጣኝም ከሆንኩም ጀምሮ ኢትዮጵያ ቡና የሆነ ነገር ሊኖረው ይገባል ብዬ አስባለው። እያደገ ሊሄድ ሊታረም የሚችል ከታች የሚመጡ ታዳጊዎች በእዛ ሂደት እየተነካኩ የሚያልፉበት አንድ የራሱ የሆነ ነገር ሊኖረው እንደሚገባ አስባለው። የእኔ አሁን ዋናው ትኩረቴ ይሄን ከመስራት አንፃር ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ ያ ነገር ውጤቱን ያመጣል የሚል እምነት አለኝ። ግን አሁን እዛ ላይ ነው ትኩረት ማድረግ የምፈልገው።

ከኢትዮጵያ ከወጣህ ረጅም ዓመታት አስቆጥረሀል። ምን ያህል ስለ ኢትዮጵያ እግርኳስ ግንዛቤው አለህ? ትከታተል ነበር?

እውነት ለመናገር በተወሰነ ደረጃ የመከታተል አጋጣሚዎች ቢኖሩም በቅርበት የምከታተል አልነበርኩም። ከዚህ ውጭ የተለያዩ መረጃዎችን ከሰዎች ትወስዳለህ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጨዋታዎች በቲቪ የማየት እድል ልታገኝ ትችላለህ። በዚህ ውስጥ አሁን ስላለው የእግርኳስ ደረጃ የማየው እና የምረዳው ነገር አለ። ያም ቢሆን በደንብ በቅርበት እከታተላለው ብዬ አላስብም።

በዚሁ አጋጣሚ ስለ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ወቅታዊ ሁኔታን እናንሳ እንዴት ታየዋለህ። በየዓመቱ እያደረገ የሚገኘውን ጉዞ?

ቅድም ካልኩህ የተለየ ነገር አይኖርም። በመጀመርያ ቁጭ ብለን ማሰብ አለብን። አሁን ባለው ተጫዋች አቅም የት ድረስ ነው መሄድ የምንችለው የሚለውን ነገር ማሰብ ያስፈልጋል። በግምት መጫወት የለብንም፤ አቅማችንን ማወቅ ያስፈልጋል። ከዚህ በፊት የተናገርኩት አንድ የማስታውሰው ነገር አለ። ሥም ከበደ ከተናገረው ጋር ተያይዞ (ሥዩም ይሄንን ብሏል አላለም እርግጠኛ አይደለሁም።) የጊዮርጊስን ቡድን ይዞ ቱኒዚያ ሄዶ የክለብ ጨዋታ ነው። ከተሸነፉ በኃላ አቅማችን እዚህ ድረስ ነው በማለት ያስቀመጠው ነገር አለ። ጥሩ ነው አቅማችን የት ድረስ እንደሆነ ማወቅ መልስ ለመስጠት ያስችልሀል። እኔ መጀመርያ በትክክል የተጫዋቾቻችን አቅም የት ድረስ ነው የሚለውን ማወቅ ያስፈልጋል። ከዛም በኃላ የእኛ ተጫዋቾችን አቅም ከተረዳህ በኃላ በእኛ ልጆች አቅም የኳስ ጨዋታ ባህሪው የሚጠይቀውን ነገር መልስ መስጠት ይቻላል። የተጋጣሚ ቡድን የምትከተለው አጨዋወት ቢያንስ ከጨዋታው አስቀድሞ መቶ ፐርሰንት እንዲህ ነው ማለት ባትችልም ሰማንያ፣ ሰባ ፐርሰት የእኔ ቡድን እዚህ ድረስ መሄድ ይችላል ብሎ መናገር ይቻላል። ምክንያቱም በየጊዜው የምታየው እና የምትሰማው ነገር ብሔራዊ ቡድን አንድ ጊዜ ጥሩ ነው ይባላል። አንዳዴ ጥሩ አይንቀሳቀስም ይላሉ። ጥሩ ያልሆኑበትን ነገር ማየት ያስፈልጋል። እኔ እውነት እንነጋገር ከተባለ ብዙ የማስበው ነገር አለ። ግን ያንን ነገር ማየት ያስፈልጋል ብዬ ነው የማስበው።

የመጨረሻ ጥያቄ ላድርገውና ሰማንያ ፐርሰት ከኢትዮጵያ ቡና ጋር አብሮ ለመስራት ከስምምነት እንደረስክ እና ገና ፊርማህን እንዳላኖርክ ቅድም ጠቁመኸኛል። ያም ቢሆን በቀጣይ ዓመት ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ምን መስራት ማሳካት ትፈልጋለህ ዕቅድ ብትገልፅልኝ ?

እኔ አሁን ጠቅለል ያለ ነገር ነው የማስቀምጠው። ስለ ቀጣይ ነገር አሁን ብዙ የምለው ነገር የለም። ቅድም ያልኩህን ነገሮች ማድረግ ከተቻለ ከዛ በኃላ ያሉ ነገሮች አስቸጋሪ አይሆኑም። ከታች ያሉ ተጫዋቾችን መተካቱ አስቸጋሪ አይሆንም፣ እንደገና ስህተትን እያረምክ ቡድኑን የተሻለ ደረጃ ማምጣት አስቸጋሪ አይሆንም። የመጀመርያው ጊዜ ላይ የምታስበውን ሀሳብ ለማምጣት የምትፈልገውን ሀሳብ ወደ ቡድኑ ለማውረድ አስቸጋሪ፣ ከባድ እና ፈታኝ ሊሆን ይችላል። ግን ያንን ነገር ማድረግ ከተቻለ በሂደት ቡድኑ ላይ ውጤታማ እንዲሆን ማድረግ ይቻላል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡