ሻሼ አካዳሚ የእግርኳስ ቁሳቁሶች ድጋፍ ተደረገለት

በሻሸመኔ ከተማ ከ70 በላይ ከ6-15 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ታዳጊዎችን በማቀፍ በቀድሞ እውቅ ተጫዋች መስፍን አህመድ መስራችነት ለሚመራው” ሻሼ አካዳሚ” የእግርኳስ ቁሳቁስ ድጋፍ ተበረከተለት።

በቅርብ ዓመት ውስጥ እግርኳስን ከማቆሙ አስቀድሞ በኢትዮጵያ መድን፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና መከላከያ በአጥቂ መስመር ተጫዋችነቱ የምናቀው እና ከባንክና መከላከያ ጋር የኢትዮጵያ ዋንጫ ማንሳት የቻለው ስኬታማው ተጫዋች መስፍን አህመድ (ጢቃሶ) በትውልድ ከተማው ሻሸመኔ “ሻሼ” የተሰኘ አካዳሚ ከአራት ወር በፊት በመክፈት ታዳጊዎችን እያሰለጠነ ይገኛል።

በእግርኳስ ተጫዋችነት ህይወቱ ያገኘውን ልምድ ለተተኪው ትውልድ ለማስተላለፍ በማሰብ በመሠረተው በዚህ አካዳሚ ከእርሱ ጋር በመሆን ኤፍሬም ዓለምነህ፣ አንዷለም ረድኤቱ እና ተስፋ ይፍሩ አብረውት የሚሰሩ ሲሆን መሠረታዊ የሆኑ የእግርኳስ ስልጠናዎችን በአካዳሚው እየሠጠ ይገኛል።

ይህን ትልቅ አላማ ለመደገፍ ኑሮውን በአሜሪካ ያደረገው እና ቤተሰብ ለመጠየቅ ወደ ትውልድ ሀገሩ ሻሸመኔ በመጣበት አጋጣሚ አካዳሚውን በመጎብኘት በግል ተነሳሽነት አቶ ትህትና ታዬ በተባለ ግለሰብ አማካኝነት የእግርኳስ መጫወቻ ኳሶች እና የተለያዩ የልምምድ ቁሳቁሶችን ድጋፍ ተደርጎለታል።

የአካዳሚው መስራች መስፍን ሲናገር ” ይህንን አካዳሚ በመጎብኘት ድጋፍ ላደረገልን ለወጣት ትህትና ምስጋናችንን እያቀረብን ይህን ትልቅ ራዕይ የያዘን አካዳሚ ወደ ፊት ብዙ ተስፈኛ ተጫዋቾችን እንዲያፈራ ወላጆች ከሚያደርጉልን ድጋፍ ባሻገር መሰል ባለሀብቶች እና የክልሉ አመራሮች ድጋፍ ሊያደርጉ ይገባል። በተለይ ታዳጊዎቹን ልምምድ የምናሰራበት ሜዳ የተቸገርን በመሆኑ የሚመለከታቸው አካላት ይህ ችግራችን እንዲቀርፉልን እንጠይቃለን።” ብሏል።

እንደነዚህ ያሉ በእግርኳሱ ያለፉ የቀድሞ ተጫዋቾች በግል ተነሳሽነት አካዳሚ መክፈታቸው የሚያበረታታ በመሆኑ እግርኳሱን የሚወዱ አቅም ያላቸው ግለሰቦች፣ ተቋማት ድጋፍ በማድረግ ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አንናስገነዝባለን።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡