ኳታር 2022| የኢትዮጵያ ተጋጣሚ አዲስ አሰልጣኝ ቀጠረች

በቀጣይ ሳምንት በዓለም ዋንጫ ማጣርያ ኢትዮጵያን የምትገጥመው ሌሶቶ አዲስ አሰልጣኝ ቀጥራለች።

በዋና አሰልጣኙ ሞሰስ ማሊሄ ህመም ምክንያት በብሄራዊ ቡድኑ ቴክኒካል ዳይሬክተር ሌስሊ ኖትሲ አማካኝነት ለዓለም ዋንጫው የማጣርያ ጨዋታ የተጫዋቾች ምርጫ ያካሄዱት ሌሶቶዎች በህመም ምክንያት መቀጠል ባልቻሉት ሞሰስ ማሌሄ ምትክ ደቡብ አፍሪካዊው የ38 ዓመት ወጣት አሰልጣኝ ታቦ ሴኖንግን ዋና አሰልጣኝ አድርገው ቀጥረዋል።

ከዚህ በፊት በደቡብ አፍሪካ ከ20 ዓመት በታች በዋና አሰልጣኝነት እና በማምሎዲ ሰንዳውንስ የውጤታማው አሰልጣኝ ፒትሶ ሞሲሜኔ ምክትል ሆኖ የሰራው ይህ ወጣት አሰልጣኝ የሌሶቶው ስራ በእግር ኳስ ህይወቱ ትልቁ ሹመቱ ሲሆን ስራውም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን በመግጠም ይጀምራል።

አብዛኛው የአሰልጣኝነት ጊዜውን ምክትል ሆኖ የሰራው አሰልጣኙ ከላይ ከተጠቀሱት ስራዎች ውጪ በደቡብ አፍሪካ ብሄራዊ ቡድን በተለያየ ጊዜ የስትዋርት ባክስተር እና የኤፍሬም ማሻባ ምክትል በመሆን ሰርቷል።


© ሶከር ኢትዮጵያ