ከፍተኛ ሊግ | ዲላ አዳዲስ ተጫዋቾችን ሲያስፈርም የስያሜ ለውጥ ማድረጉንም አሳውቋል

ደረጀ በላይን በዋና አሰልጣኝነት የቀጠረው ዲላ ከተማ አዳዲስ ተጫዋቾች ወደ ቡድኑ መቀላቀል ጀምሯል።

በኢትዮጵያ እግርኳስ ታሪክ ለበርካታ ጊዜ ከቡድኖች ጋር ወደ ፕሪምየር ሊግ በማደግ ከሚጠቀሱ ተጫዋቾች አንዱ የሆነው ሰለሞን ብሩ ዲላን ተቀላቅሏል። ሰለሞን በዳሽን ቢራ፣ ወሎ ኮምቦልቻ፣ ደደቢት፣ ጅማ አባጅፋር፣ ባህር ዳር እንዲሁም ወልቂጤ ከተማ የተጫወተ ሲሆን ከደደቢት እና ወሎ ኮምቦልቻ በቀር አራቱ ቡድኖች ወደ ፕሪምየር ሊግ ሲያድጉ የየቡድኖቹ አባል ነበር።

ከወልቂጤ አማካዩ ሀምዲ ሶፊ ሌላኛው ቡድኑን የተቀላቀለ ተጫዋች ሲሆን ከዚህ ቀደም በዲላ ሲጫወት የነበረው መና በቀለ ከኢኮስኮ ወደ ቀድሞ ቡድኑ ተመልሷል። ከቤንች ማጂ ቡናም የተከላካይ አማካዩ ዳንኤል ቡድኑን ተቀላቅሏል።

በተያያዘ ዜና ዲላ ከተማ ለእግርኳስ ፌዴሬሽን ባሳወቀው መሰረት የክለቡን ስያሜ ወደ ጌዴኦ ዲላ መቀየሩን የቡድኑ ሥራ አስኪያጅ አቶ ተዘራ ጌታሁን ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል። “ቡድኑ ሥያሜውን ከዲላ ከተማ ወደ ጌዴኦ ዲላ ከቀየረ ቆየት ብሏል። ይህን ካሳወቅን ቆየት ብንልም አንዳድንድ ሚዲያዎች በዲላ ከተማ ነው የሚጠሩት፤ ይህ መስተካከል አለበት። ስፖርቱ በዞኑ ያሉትን ሁሉንም አካላት ማሳተፍ ስላለበት እና የኔነት ስሜት ይበልጥ ለመፍጠር በማሰብ የስያሜ ለውጥ ማድረግ አስፈልጓል።” በማለት ዲላ ከተማ ወደ ጌዴኦ ዲላ የስያሜ ለውጥ ማድረጉን ገልፀዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ