በ2022 በኳታር አዘጋጅነት ለሚካሄደው የዓለም ዋንጫ ቅድመ ማጣሪያ ከሌሶቶ ጋር ነሐሴ 29 ባህር ዳር ላይ የሚጫወቱት ዋሊያዎቹ አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ቡድኑ እየቀላቀሉ ይገኛል።
ጨዋታውን በሚያደርጉበት ባህር ዳር ከተማ በአሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ እየተመሩ ዝግጅታቸውን እያደረጉ የሚገኙት ዋልያዎቹ ባልተሟላ ሁኔታ ዝግጅታቸውን ቢጀምሩም በውጭ እና በሀገር ውስጥ የሚገኙ ጥሪ የተደረገላቸው ተጫዋቾች ቡድኑን መቀላቀል በመጀመራቸው በተሟላ ሁኔታ ጠንካራ ያለ ዝግጅታቸውን እያደረጉ ይገኛል።
በኖርዌይ የሚጫወቱት አሚን አስካር እና ዳንኤል ተሰማ እንዲሁም በጀርመን እየተጫወተ የሚገኘው ካሊድ ሙሉጌታ ከፓስፖርት እና ከሌሎች ጉዳዮች ጋር ተያይዞ ለጨዋታው የመድረሳቸው ነገር አጠራጣሪ በመሆኑ እንዲሁም የፋሲል ከነማው የግራ መስመር ተከላካይ አምሳሉ ጥላሁን በጉዳት ምክንያት ወደ ቡድኑ እስካሁን ያልተቀለ በመሆኑ አሰልጣኝ አብርሃም በጎደሉት ተጫዋቾች ምትክ ሌሎች አማራጮችን መከተል ጀምረዋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በብሔራዊ ቡድኑ ጥሪ ቀርቦለት እየተጫወተ የሚገኘው እና በዚህኛው የተጫዋቾች ጥሪ ላይ ያልተካተተው የሰበታው የቀኝ መስመር ተከላካይ ጌቱ ኃ/ማርያም በድጋሚ ጥሪ ተደርጎለታል። ለግብፁ ምስር ኤል ማቃሳ የሚጫወተው ሽመልስ በቀለ እና ለሲዊድኑ ክለብ ስሪያንስካ የሚጫወተው ቢንያም በላይም ብሔራዊ ቡድኑን ተቀላቅለው ዛሬ ልምምድ ጀምረዋል።
በቀሩት ቀናት አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ ሌሎች ተጫዋቾችን ጥሪ ስለማድረጋቸው ባይታወቅም በቅርቡ ለግብፁ ሃራስ ኤል ሆዳድ ፊርማውን ያኖረው ጋቶች ፓኖም ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር በቀጣይ ቀናት ይቀላቀላል ተብሎ የሚጠበቅ ብቸኛው ተጫዋች ሆኗል።
© ሶከር ኢትዮጵያ