በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት የከፍተኛ ሊግ ቻምፒዮን በመሆን ወደ ፕሪምየር ሊጉ ቢያድግም በመጣበት ዓመት ከሊጉ በመውረዱ ክለቡን ሊያፈርስ እንደሆነ ተነግሮ የነበረው ደቡብ ፖሊስ በቅርቡ ራሱን አጠናክሮ ዳግም ለመቅረብ እንደተዘጋጀ ተገልጿል።
በመጣበት ዓመት ወደ ከፍተኛ ሊግ የወረደው ክለቡ ወልዋሎ ከስሑል ሽረ በነበረው የ29ኛ ሳምንት ጨዋታ ላይ ቅሬታ አለኝ በማለት ከመከላከያ ጋር ለፌዴሬሽኑ ደብዳቤን ማስገባቱ ይታወሳል። ምላሽ ካልተሰጠኝም ከፌዴሬሽኑ ጋር አብሬ መስራት ስለማልችል ለማፍረስ እገደዳለሁ በማለት የገለፀ ቢሆንም ዳግም ወደ ውድድር ለመመለስ እና በተሻለ ጠንካራ ሆኖ ለመቅረብ ማሰቡን የክለቡ የቦርድ አባል ኢንስፔክተር እታገኝ ዜና በተለይ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፃለች። “ፌዴሬሽኑ ያስገባነውን ቅሬታ ተመልክቶ እስከ አሁን በፕሪምየር ሊጉ ወይም በከፍተኛ ሊጉ ትሳተፋላቹ ብሎ ያሳወቀን ነገር የለም። ያንን ተንተርሰን ቅሬታ አሰምተን ነበር። የሆነው ሆኖ ይህ ክለብ ትልቅ ታሪክ ያለው በመሆኑ በበለጠ ተጠናክሮ ለመምጣት ቅድመ ዝግጅት ላይ ነን።”
ኢንስፔክተር እታገኝ ጨምራ እንደገለፀችውም በቅርቡ የአሰልጣኝ ቅጥር ይከናወናል።”ከዚህ በፊት ማስተካከል የነበሩብን የውስጥ ችግሮች ነበሩ። እነሱን ለቀጣይ እንዳይኖሩ እያስተካከለልን እንገኛለን። ነባር የአሰልጣኝ ቡድን አባላትን ጠርተን ከትላንት ወዲያ ተወያይተናል። ለክለቡ የሚሆን አሰልጣኝ ካመጣን በኋላ በቅርቡ ወደ ተጫዋቾች ምልመላ ገብተን አዳዲስ ተጫዋቾችን እናስፈርማለን።” ብላለች።
© ሶከር ኢትዮጵያ