በከፍተኛ ሊግ እና አንደኛ ሊግ ተጫዋቾች ላይ የደሞዝ ጣሪያ ተወሰነ

የከፍተኛ ሊግ እና አንደኛ ሊግ የተጫዋቾች ደሞዝ ጣርያን ለመወሰን ከ14 ቀን በፊት ዓለምገና ከተማ እንኮር ሆቴል በሚገኘው አዳራሽ ሊካሄድ የነበረው ስብሰባ በምዕላተ ጉባዔ አለመሟላት ምክንያት ለዛሬ ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቶ መበተኑ የሚታወስ ሲሆን በዛሬው ዕለት ስብሰባው ተከናውኖ የደሞዝ ጣርያ ተወስኗል።

በዋቢ ሸበሌ አዳራሽ ጠዋት 3:00 ላይ የተጠራው ስብሰባ ዘግይቶ የጀመረ ሲሆን ከ90% በላይ የሁለቱም ሊግ የክለብ አመራሮች በተገኙበት ስብሰባ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ባህሩ ጥላሁን በመርሐ ግብሩ ይዘት ዙርያ ገለፃ ከተደረገ በኋላ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፊዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ የእንኳን ደህና መጣቹ ንግግር አድርገዋል።

ፕሬዝዳንቱ በንግግራቸው ሁለት ነገሮችን በአትኩሮት እንደሚሰሩ ገልፀዋል። በአንደኝነት ቡድኖቹ ያስቀመጡትን የደሞዝ ጣሪያ ፌዴሬሽኑ ቁጥጥር እንደሚያደርግበት እንዲሁም በቀጣይ የ2012 ውድድር ዓመት ውድድሩ መቼ እንደሚጀመር በቅርቡ እንደሚሳውቁ ገለፃ ካደረጉ በኋላ ፌዴሬሽኑ ቡድኖች የሚጠቀሙት የመንግስት ገንዘብን መሆኑ ታውቆ አላስፈላጊ መንገድ እየሄደ ያለው የደሞዝ ጉዳይ ልጓም ሊበጅለት እንደሚገባ በአፅኖት ተናግረዋል። በስተመጨረም እያንዳንዱ የቡድን አመራሮች ውሳኔያቸውን ከሀገራቸው ነባራዊ እና ተጫባጭ ሁኔታ ተመስርተው እንዲወስኑ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ከፕሬዝዳንቱ በመቀጠል አቶ ተድላ እና ቴዎድሮስ በክፍያ ሁኔታ ዙርያ ጥናታዊ ፅሁፍ አቅርበዋል። በጥናታዊ ፅሁፉ የሌሎች ሀገር ተሞክሮ፣ የገንዘብ ፍሰቶችን እንዴት መቆጣጠር እንደሚቻል፣ ቡድኖች ሊያሟላቸው የሚገቡ መሰረታዊ ጉዳዮች፣ በቀጣይ በክለብ ላይሰንስ ማሟለት ያለባቸው ነገሮች፣ የከፍተኛ እንዲሁም ዝቅተኛ ክፍያ የሚመጣውን ተፅእኖ፣ ቡድኖች መቼ ከፍተኛ ከፋይ መሆን ይችላሉ የሚሉ ርእሰ ጉዳዮችን አቅርበዋል። በጥናቱም ወቅት የከፍተኛ ሊግ ቡድኖች ከፍተኛ ክፋይ እና ዝቅተኛ ክፍያ ከፍተኛው 100,000 ብር ዝቅተኛው ደሞ 5000 ብር መሆኑ ከተገለፀ በኋላ የከፍተኛ ሊግ ቡድኖች በሁለት ቡድን በመክፈል እንዲሁም አንደኛ ሊግን ተመሳሳይ ሁኔታ በቡድን ውይይት እንዲያደርጉ የተደረገ ሲሆን በውይይቱም ከሀገር፣ ከተጫዋች እንዲሁም ከቡድን አንጻር እንዲመለከቱት ከዚህ በተጨማሪ ቡድኖች ሊጋጥሙ የሚችሉትን ተግዳሮቶች እንዲወያዩበት መድረክ ተፈጥሯል።

ከውይይቱ በኋላ ከሀገር አንፃር ኢኮኖሚውን በመጥቀም ያልተገባ የሀብት ብክነትን በመከላከል እና ፍትሀዊ የሀብት ክፍፍል እንዲኖር፣ ከተጫዋች አንፃር ለታዳጊዎች እድል እንዲሰጥ እንዲሁም ፍትሀዊ የሆነ የክፍያ መጠን እንዲኖር፤ ከቡድን አንፃር ቡድኖች ለታዳጊዎች እድል መስጠት እንዲችሉ እና አካዳሚ እንዲመሰርቱ እንዲሁም ህዝባዊ መሰረት እንዲይዙ ይረዳል ተብሏል።

በስተመጨረሻም የከፍተኛ ሊግ እና የአንደኛ ሊግ ተሳሳታፊ አካላት የተጫዋች የደሞዝ መጠኑን ወስነዋል። በዚህም ከፍተኛ ሊግ 20,000 ብር፣ አንደኛ ሊግ ደግሞ 5000 ብር እንዲሆን ተወስኗል። ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራም የተለየ ሀሳብ ካለ ጠይቀው ቤቱ በክፍያው በመስማማቱ በቃለ ጉባዔ ላይ ፊርማቸውን እንዲያኖሩ ጠይቀው ህጉ ተፈፃሚ እንደሚሆን እና ከዚህ በፊት ውል የነበራቸው ተጫዋቾችን የማይመለከት መሆኑን ጨምረው ገልፀዋል። 

.


© ሶከር ኢትዮጵያ