“የደሞዝ መመርያውን ለማስከበር ጠንክረን እንሰራለን” ኢሳይያስ ጂራ

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በፕሪምየር ሊግ ተጫዋቾች ላይ ከሁለት ሳምንታት በፊት የደሞዝ ጣርያ ማስቀመጡ የሚታወስ ሲሆን በዛሬው ዕለት ደግሞ የከፍተኛ ሊግ እና አንደኛ ሊግ ተጫዋቾች ላይ ውሳኔ አሳልፏል።

ፌዴሬሽኑ ከውሳኔው ተፈፃሚነት ጋር በተያያዘ ትላንት የሚመለከታቸው አካላትን ማስጠንቀቁ የሚታወስ ሲሆን የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ ጋራ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረጉት ቆይታ መመርያውን ለማስከበር እየሰሩ መሆኑን ገልፀዋል።

የፕሬዝዳንቱን ሀሳብ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡-

“የደሞዙ ወቅታዊ ሁኔታ ጤናማ ነው፤ አይደለም ለማለት ትንሽ ጊዜ ይጠይቃል። እስካሁን ፌዴሬሽኑ ጋር የገቡ ሰነዶች በ50,000 ብር ጣሪያ እንደፈራረሙ ነው ያለው። ነገር ግን እኔም እንደሌላው ድርድሩ እና ክፍያው ከዚያ በላይ እንደሆነ ሰምቻለሁ። በሚቀጥለው ሳምንት በዚህ ዙሪያ ላይ የተዘጋጀ ደንብ እና መመሪያዎች ለሁሉም ክለቦች ይደርሳል። ፌዴሬሽኑም የተወሰነውን ውሳኔ ያስፈፅማል።

“የሚወሰደው እርምጃ ቡድኖችን ከውድድር መሰረዝ ሳይሆን ከፍተኛ የገንዘብ ቅጣት መጣል ነው። በተጨማሪም የፈረመውን ተጫዋች ግልጋሎት አያገኙም። ፌዴሬሽኑ ከሚመለከተው የመንግስት አካል ጋር ዝግጅቱን አጠናቋል። በማንኛውም ሰዓት ጥቆማ ሲደርሰው ከፀረ ሙስና እና ከፌዴራል ፖሊስ ጋር በመሆን ጥቆማውን የሚምርምር እና የሚያጠና ይሆናል። ጉዳዩን የፈፀሙት አካላትም በወንጀለኛ ህግ እስከመጠየቅ ይደርሳሉ። እንዲሁም ገቢዎች ሚኒስቴር ተገቢውን ግብር ወደጎን በማድረግ ላሸሹበት በከፍተኛ ወንጀል የሚጠይቅበት አሰራር ተዘርግቶ አልቋል። በማንኛውንም ገንዘብ ልውውጦች ተገቢውን ግብር መንግስት ማግኘት አለበት። ከመንግስት ዝርፊያ የሚፈፅሙ አካላቶችን በህግ ይጠያቃሉ። ከዚህም በኋላ ማንኛውም ቡድን በገቢዎች ሚንስትር የፋይናንስ ፍተሻ ይደረግበታል። ሂሳቡን ሲፈርም ሆነ ሲወስን የነበረው እንዲሁም የተቀበለው አካል ተጠያቂ የሚደርግበት ህግ ተግባራዊ ይሆናል።

” በስተመጨረሻ የማስተላልፈው መልዕክት እንዲህ እያደረጉ ያሉ ቡድኖች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡና እንዲጠነቀቁ ነው። እነሱ እና ቡድኑ ብቻ ሳይሆን ቤተሰቦቻቸው በውሳኔው ይጎዳሉ። የህግ የበላይነት ለማስፈን እና መመሪያው እንዲከበር ጠንክረን እንሰራለን። ብቻችንን ሳይሆን ከሁሉም የመንግስት አካላት ጋር እንደምሰራ መታወቅ አለበት። ”


© ሶከር ኢትዮጵያ