የሽረ ስታዲየም እድሳት ተጀመረ

የፕሪምየር ሊጉ ክለብ ስሑል ሽረ የሚጠቀምበት የሽረ እንዳሥላሴ ስታዲየምን የመጫወቻ ሜዳ ሣር የማልበስ ሥራ ሲጀመር ቡድኑም የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን ጀምሯል። 

ከአንድ ወር ገደማ ቀደም ብሎ የእድሳት ስራው ይጀመራል ተብሎ በተለያዩ ምክንያቶች ሳይጀመር የቆየው ይህ የስታዲየም እድሳት ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ቅድመ ስራዎች ተጀምረውበታል። እስከ ጥቅምት መጨረሻ ድረስ የሣር እና ተያያዥ ስራዎች ያጠናቅቃል የተባለለት ሜዳው ለቀጣይ ዓመት ጨዋታዎች ለማስተናገድ እንዲያስችል ቶሎ ለማጠናቀቅ እንደታሰበ ከክለቡ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በሌላ ዜና ባለፈው የውድድር ዓመት በመጨረሻው ሳምንት በሊጉ መቆየታቸውን ያረጋገጡት ስሑል ሽረዎች ዛሬ በትግራይ ስታዲየም የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን ጀምረዋል። በዝውውር መስኮቱ በረከት ተሰማ እና አክሊሉ ዋለልኝን ጨምሮ የአራት ተጫዋቾች ዝውውር አጠናቀው በቀጣይ ቀናትም ተጨማሪ ተጫዋቾች ለማዘዋወር ከጫፍ የደረሱት ስሑል ሽረዎች ውላቸው የተጠናቀቁ ነባር ተጫዋቾችን ውልም ያድሳሉ ተብሎ ይጠበቃል።


© ሶከር ኢትዮጵያ