ቶኪዮ 2020| ሉሲዎቹ የመልስ ጨዋታቸውን ነገ ያደርጋሉ

የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን በቶኪዮ ለሚዘጋጀው የ2020 የኦሊምፒክ ውድድር ለማለፍ የቅድመ ማጣሪያ የመልስ ጨዋታውን ነገ ያከናውናሉ።

በ2020 ጃፓን ቶኪዮ ላይ ለሚደረገው የኦሊምፒክ ውድድር ለመሳተፍ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ እያደረጉ የሚገኙት የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን የመልስ ጨዋታቸውን ለማድረግ ካሜሩን ገብተዋል። ከሳምንት በፊት ባህር ዳር ላይ የተጫወቱት ሉሲዎቹ በተቀዛቀዘ የጨዋታ እንቅስቃሴ 1-1 መለያየታቸው ይታወሳል። 29 የልዑካን ቡድን ይዘው ከትላንት በስቲያ ወደ ካሜሩን ያመሩት ሉሲዎቹ ዛሬ ከሰዓት ጨዋታቸውን ነገ በሚያደርጉበት ኦምኒ ስፖርት ስታዲየም ልምምዳቸውን ሰርተዋል።

በነገው ጨዋታ ማሸነፍ አልያም ከሁለት ጎል በላይ አቻ መውጣት ወደ ቀጣዩ ዙር የሚያሳልፋቸው ሉሲዎቹ ከተጋጣሚያቸው ካሜሩን ብርቱ ፉክክር እንደሚጠብቃቸው ይገመታል። ከናይጀሪያ በመቀጠል ከአፍሪካ ሁለተኛዋ ሃያል ቡድን የሆነችው ካሜሩን በመጀመሪያው ጨዋታ (ባህር ዳር ላይ የተደረገው) ያልተሰለፉ ወሳኝ ተጨዋቾቿን በነገው ጨዋታ እንደምትጠቀምም ተሰምቷል።

ጨዋታው ነገ 11:30 በኦምኒ ስፖርት ስታዲየም ይከናወናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ