ፊሊፕ ኦቮኖ ማረፍያውን በቅርቡ እንደሚያውቅ ከደቡብ አፍሪካው ድረ ገፅ ጋር ባደረገው ቆይታ ተናግሯል።
በመቐለ 70 እንደርታ የሁለት ዓመት ቆይታው እጅግ ድንቅ ብቃት በማሳየት በደጋፊዎች ከፍተኛ ተወዳጅነት ያተረፈው እና ቡድኑ የፕሪምየር ሊግ ዋንጫ እንዲያነሳ ከፍተኛ ድርሻ የነበረው ፍሊፕ ኦቮኖ ከደቡብ አፍሪካው ‘ኪክ ኦፍ’ ድረገፅ ጋር ባደረገው ቆይታ ከደቡብ አፍሪካ ክለቦች ጥያቄ ከቀረበለት ለመቀበል ዝግጁ መሆኑን ገልፆ ከቅዱስ ጊዮርጊስ የቀረበለት የዝውውር ጥያቄ እንዳለ የተናገረ ሲሆን በደቡብ አፍሪካ የታየበት ምክንያት ግን ለጉብኝት ብቻ እንደሆነ ገልጿል። “እዚህ የመጣሁት ፕሪቶርያን ለመጎብኘት ብቻ ነው። ለብሔራዊ ቡድን የማጣርያ ጨዋታ ሀገሪቷን ለቅቄ እሄዳለው (ሰኞ የብሔራዊ ቡድኑን ተቀላቅለቀል)። ሆኖም ከደቡብ አፍሪካ ክለቦች ጥሪ ከቀረበልኝ ውድቅ አላደርግም።”ብሏል ።
ኢኳቶርያል ጊኒያዊው ግብጠባቂ በቀጣይ ዓመት በመቐለ ይቆያል ወይስ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ከዚህ ቀደም ጥቂት ጊዜ ወዳሳለፈበት ደቡብ አፍሪካ ያመራል የሚለው ጉዳይ ከብሄራዊ ቡድን ጨዋታዎች መልስ ይለያል ተብሎ ይጠበቃል።
© ሶከር ኢትዮጵያ