በቶኪዮ ኦሊምፒክ የሁለተኛ ዙር ማጣሪያ የመልስ ጨዋታ ዛሬ ያውንዴ ላይ ከካሜሮን ጋር የተጫወተችው ኢትዮጵያ ያለግብ በአቻ ውጤት ብታጠናቅቅም ከሜዳ ውጪ ባገባ ካሜሩን ወደ ቀጣይ ዙር ማለፏን ካረጋገጠች በኋላ አሰልጣኝ ሰላም ዘርዓይ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርጋለች፡፡ የአሰልጣኟን አስተያየትም በሚከተለው መልኩ አቅርበነዋል፡-
“በጣም ጥሩ ጨዋታ ነበር፤ ከባህር ዳሩ ይበልጥ ፈታኝም ነበር። እነሱ በሙሉ ኃይላቸው ነበር ሲያጠቁ የነበሩት። በተወሰነ መልኩ የነሱን ያህል ባይሆን ወደ ግብ ለመጠጋት ሞክረናል። እነሱ በእኛ ሜዳ የነበራቸው ጨዋታ ዛሬ ከውጪ የተቀላቀሉ ተጫዋቾችንም ስለተጠቀሙ ጥሩ ነበሩ። በራሳችን መንገድ አሸንፎ ለመውጣት እና ግብ ለማስቆጠር ያደረግነው ጥረት እጅጉን አስደስቶኛል። በውጤት ደረጃ ተሸንፈን አይደለም የወደቅነው። ምንም እንኳን ከውድድሩ ብንወጣም ሳንሸነፍ መጨረሳችን ለቀጣዩ ጠንካራ መንገድ ያበጅልናል። ቡድኑ መቀጠል የሚችል አቅም አለው። በዛሬው ጨዋታ ካሜሩኖች በፈጣን አጨዋወት ወደ ሜዳ ቢገቡም ያን ሁሉ ተቋቁመን በመውጣታችን እና ተጫዋቾቼ ባሳዩት እንቅስቃሴ ደስተኛ ነኝ። በሌሎች ውድድሮች ተሻሽለን እንደምንቀርብ ተስፋ አለኝ።”
© ሶከር ኢትዮጵያ